በመዲናዋ ከነገ ጀምሮ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና አገር አቀፍ መድረኮች እንደሚዘጋጁ ተገለፀ

መስከረም 23/2016 (አዲስ ዋልታ ) በአዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና አገር አቀፍ መድረኮች እንደሚዘጋጁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እናትአለም መለሰ ገለፁ።

መድረኮቹ ከተማዋ ለሕጻናት ሁለንተናዊ አስተዳደግ የሚመጥኑ መሠረተ ልማቶችን እውን ለማድረግ በትኩረት እየሰራች መሆኗን ለማሳወቅ ያለመ ስለመሆኑ ሃላፊዋ ገልፀዋል።

በዚህም መስከረም 24 እና 25 የአፍሪካ ከንቲባዎች የሊደርሺፕ ኢኒሼቲቭ መድረክ፤ መስከረም 28 እና 29 የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የልህቀት ማዕከልን ለማቋቋም የሚረዳ ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክ ይጠቀሱበታል።

እንዲሁም ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 1/2016 ዓ.ም የሀገር አቀፍ መሪዎች የልምድ ልውውጥ መድረኮችን የምታስተናግድ ሲሆን፣ በዚህም ከተማዋ ሦስት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ትልልቅ መድረኮች ለማከናውን አስፈለጊ ቅድመ ዝግጅት አጠናቃለች ብለዋል።

የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ከጅምሩ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ የቻልንበት ነው ያሉት ኃላፊዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገብናቸው ውጤቶች ስኬታማነት ሀገራዊ እና አህጉራዊ ተሞኩሮ ለመሆን መቻሉን ጠቁመዋል።

እስካሁን ባለው በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም 2500 የወላጆች እና አሳዳጊዎች የምክር አገልግሎት ሰራተኞች፤ ከ56 በላይ ጤና ጣቢያዎች የቀዳማይ ልጅነት ተኮር የህጻናት እና ወላጆች ጤና ክብካቤ አግልገሎትን መስጠት፤ 6 የፌዴራል ሆስፒታል ባለሙያዎች በሕጻናትና እናቶች ላይ ብቻ ማዕከል አድርገው እንዲሰሩ የሚያስችል ስልጠና ወስደው አገልግሎት መጀመራቸውን ጨምሮ ከተማ አስተዳደሩ 9500 ለሚሆኑ ህጻናት እና ወላጆች በከተማዋ አልሚ ምግብ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል።

ይሕ በእንዲህ እንዳለ 46 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ወደ ጨዋታ መር የማስተማር ዘዴ እንዲሸጋገሩ ማስቻል፣ በከተማችን ከ 150 በላይ የመጫዎቻን ማልማት ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በቀዳማይ ልጅነት ልማት እሳቤዎች የተቃኙ 9 አዳዲስ የመጫዎች ቦታዎችም በተለያዩ አካባቢዎች ለምተው በቅርቡ አገልግሎት በመስጠት እንደሚጀምሩ ገልፀዋል።

በመግለጫቸው ማጠቃለያ ወቅት ኃላፊዋ በሦስቱም መድረኮች ከለውጡ ማግስት አንስቶ በሁሉም ረገድ የጀመርናቸው ሰው ተኮር የልማት ፕሮገራሞች እውቅና እንዲያገአኙ ከማስቻል ባለፈ ተሞክሮውን እንደ ሀገር እና አህጉር በማስፋት አህጉራዊ ተቀባይነትና ምሳሌነታችንን በተጨባጭ ለማጉላት የላቀ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነውም ሲሉ በአንክሮ መናገራቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።