ባንኩ ለማዕድን አልሚ ደንበኞች ስራ ማሳለጫ የሚያገለግሉ ማሽነሪዎችን አስረከበ


መስከረም 23/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለማዕድን አልሚ ደንበኞች ለማዕድን እና ግንባታ ግብዓት ስራ ማሳለጫ የሚያገለግሉ በ44 ሚሊዮን ብር የተገዙ 15 ሎደር ማሽነሪዎችን አስረከበ፡፡

ባንኩ በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩ ከ110 በላይ ደንበኞች ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ፋይናንስ በማድረግ ለማዕድን ልማት ዘርፉ ማደግ እየሰራ መሆኑም በርክክብ መርሃ ግብሩ ወቅት ተገልጿል።

በእለቱ ማሽነሪዎችን ያስረከቡት የልማት ባንክ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንሲንግ ምክትል ፕሬዝዳንት አስፋው አበራ ባንኩ የማዕድን ዘርፍ ልማትን በመደገፍ ለሀገራዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

መንግስት የዘርፉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በተለይም ወርቅ፣ እምነበረድና የተለያዩ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ አበረታች ውጤቶች መታየታቸው በዘርፉ ጠንክረን ብንሰራ በኢኮኖሚያችን ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት እንደምንችል አመላካች ነው ብለዋል፡፡

ለማዕድል ልማት የሚያግዙ ማሽነሪ አቅራቢ የሆኑት አብይ አበበ በበኩላቸው ሀገራችን እምቅ የማዕድን ሀብት ያላት በመሆኑ በዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ባንኩ ዘመናዊ ማሽነሪዎችን ለደንበኞቹ ማቅረቡ ኢኮኖሚው እንዲያድግ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣና በስራ እድል ፈጠራም ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ባንኩ ያቀረባቸውን ሎደር ማሽኖችን ለመረከብ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ደንበኞች በበኩላቸው በየአካባቢያቸው የሚገኙ ማዕድናትን ለማልማት የማሽኖቹ መኖር ወሳኝ መሆኑን መናገራቸውን ከልማት ባንክ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡