በመዲናዋ የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈጥሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

ነሃሴ 14/2013 (ዋልታ) –  የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ሰው ሰራሽ የምርት አቅርቦት እጥረት በሚፈጥሩና የህዝቡን የተረጋጋ ኑሮ ለማወክ ብሎም ሃገር ለማፍረስ በሚሰሩና እንዲሁም በሚተባበሩ የህዝብና የሃገር ጠላቶች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰታወቁት ዛሬ ይህንን ተግባር በበላይነት የሚመራና የሚከታተል በፌዴራል መንግስት እና በከተማ አስተዳደሩ የተዋቀረ ግብረሃይል ተቋቁሟል፡፡

በመሆኑም መላው የመዲናዋ ነዋሪ በዚህ ህገወጥ ተግባር ላይ እየተሳተፉ ያሉ ተቋማትና ግለሰቦችን በመጠቆምና በማጋለጥ እንደከዚህ ቀደሙ አብሮ እንዲሰራ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ጥሪ አቅርበዋል።