በመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ አስፈላጊነት ላይ ውይይት ተደረገ

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ አስፈላጊነት ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ከፈቃድ እና ምዝገባ ጋር ተያይዞ ረቂቅ አዋጁ ገለልተኛ ሆኖ ሚዲያውን  መከታተል እና የመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነትን  ማረጋገጥ የሚቻልበትን መንገድ አትቷል፡፡

መገናኛ ብዙሃን ከተቀመጠው መርህ ውጭ ሆነው ሲሰሩ ሊወሰድባቸው የሚገባውን እርምጃም የተመለከተው ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በፊት ያልነበረውን የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን የህግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

በህገ መንግስቱ እውቅና የተሰጠውን የሚዲያ ነጻነት ተቋማዊ እና ህጋዊ መብት እንዲኖረው ለማስቻል በረቂቅ አዋጁ ውስጥ በዝርዝር የተካተተ ሲሆን የሚዲያ ተቋማት መብትን አጠናክሮ ለማስቀጠል አዋጁ ጉልህ ሚና አለው ተብሏል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ነጻነታቸውን ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውንም በማወቅ ለህጻናት የማይመጥኑ መርሃ ግብሮች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ረቂቁ አመላክቷል፡፡

ረቂቁ ወደ ፊት ከሚመጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር አጣምሮ ለማስቀጠል በሚያስችል መልኩ እንደተዘጋጀም ተገልጿል፡፡

ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ በጠቅላይ አቃቤ ህግ የተቋቋመ አጥኚ ቡድን፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡

(በሜሮን መስፍን)