በምሥራቅ ወለጋ ዞን ከ114 ሚሊየን የሚበልጥ የቡና ችግኝ ተዘጋጀ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – የምሥራቅ ወለጋ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከል ከ114 ሚሊየን የሚበልጥ የቡና ችግኝ መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡
በዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የቡና፣ የቅመማ ቅመም እና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አቶ አሰፋ መኮንን አርሶ አደሩ በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ ያረጀውን ቡና በማስወገድ ምርታማነት የሚጨምሩና በሽታን የሚቋቋሙ የቡና ችግኞችን ሲተክል መቆየቱን ተናግረዋል።
በመጪው ክረምትም በሽታን ተቋቁሞ ምርት የሚሰጥ ከ114 ሚሊየን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን ገልጸው፣ ችግኙ የተዘጋጀው በ11ሺህ የመንግሥት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ደርጅቶችና የግል ችግኝ ጣቢያዎች እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ይህም በአዲስ መሬት እና ነባር ይዞታዎች ላይ የሚተከል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በማሳቸው ቡናን ከማልማት ባሻገር ችግኙን ለገበያ እያቀረቡ ገቢያቸውን እያሳደጉ ያሉ አርሶ አደሮችም መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ከአርሶ አደሮቹ መካከል በሳሲጋ ወረዳ የጌላ ቀርሳ ቀበሌ ነዋሪ ጌታቸው ኢዶሳ በሰጡት አስተያየት፣ ለመጪው ክረምት በግላቸው 150 ሺህ የቡና ችግኝን በማዘጋጀት እየተንከባከቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ያዘጋጁትን የቡና ችግኝ ለገበያ አቅርበው በመሸጥ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ማቀዳቸውንም ገልጸዋል፡፡
በወረዳው የሀሮ ጉዲና ቀበሌ አርሶ አደር ጥሩነህ ኡልፊና በበኩላቸው፣ ባለፈው ዓመት ከቡና ችግኝ ሽያጭ 15 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህ ዓመትም 20ሺህ የቡና ችግኞችን በማዘጋጀት ከሽያጩ ተጨማሪ ገቢ እንደሚጠብቁ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡