ወደ ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ከሚገቡ 100 ሰዎች 79 ያህሉ ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ናቸው ተባለ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – በአሁኑ ሰዓት ወደ ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ግለሰቦች 79 የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በኮቪድ-19 የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የገለጸው ኢንስቲትዩቱ፣ “በተለያየ አጋጣሚ ከሚያገኟቸው ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ ኮቪድ-19 ሊኖርበት ይችላል” ብሏል።

ለአብነትም ትናንት ለኮቪድ-19 ምርመራ ናሙና ከሰጡ 7 ሺህ 659 ግለሰቦች መካከል 1 ሺህ 981 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው መረጋገጡን ገልጿል።

በዕለቱ የምርመራ ውጤት መሰረት ከተመረመሩት መካከል ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች በመቶኛ ሲሰላ ሲዳማ ክልል 67 በመቶ፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 43 በመቶ፣ ኦሮሚያ ክልል 42 በመቶ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 25 በመቶ በማስመዝገብ ከፍተኛ ስርጭት የታየባቸው ሆነዋል።

በአዲስ አበባ የሚደረጉ የኮቪድ-19 የላቦራቶሪ ምርመራ በማህበረሰብ ቅኝት እና ዳሰሳ፣ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ የኮቪድ-19 ናሙና ምርመራ የሚያደርጉ ግለሰቦችን ያጠቃለለ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

እስከ ትናንትናው ዕለት 752 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ቫይረስ ተይዘው በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ወደ ፅኑ ህሙማን መርጃ ክፍል ገብተው በፅኑ ህክምና ማዕከል ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆናቸውን ጠቁሟል።

“በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ደግሞ 94 ግለሰቦች በሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ እየተነፈሱ የሚገኙ ናቸው” ብሏል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የነበረው ከፍተኛ የታማሚ ቁጥር 81 እንደነበር አስታውሶ፣ “በአሁኑ ሰአት ወደ ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ግለሰቦች 79 የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ናቸው” ብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው ሳምንት ወደ ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚፈልጉ ግለሰቦች 61 ሆኖ ተመዝግቦ እንደነበርም ጠቅሷል።

ወረርሽኙ እየተስፋፋ በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን ማስክን በሚገባ ማድረግ፣ ሁልጊዜ የእጆቻችንን ንጽሕና መጠበቅ፣ ከሰዎች ጋር ያለንን ርቀት መጠበቅና ሊፈጠሩ ከሚችሉ የሰዎች መሰባሰብ ራስን መቆጠብ እንደሚገባ አስገንዝቧል።

በራስ፣ በቤተሰብ፣ በጎረቤት እና በማሕበረሰብ ላይ ሊደረስ የሚችለውን የሰው ሕይዎት ሕልፈት፣ ማሕበራዊና ስነ-ልቡናዊ ቀውስ እንዲሁም ማሕበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮችን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ በመሆኑንና እያንዳንዱ ግለሰብና ተቋም በኃላፊነት ስሜት ቤተሰቡን ብሎም አገሩን የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ በመተግበር እና በማስተግበር የወረርሽኙን የስርጭት መጠን እንዲገታ ኢንስቲትዩቱ ጥሪ አቅርቧል። መረጃውን ያገኘነው ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው፡፡