በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በዞኑ ነዋሪዎች ድጋፍ መደረጉ ተገለፀ

ሚያዚያ 01/ 2013 (ዋልታ) – ከሰሞኑ በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገምቤል ወረዳ ቦኒ ቀበሌ ንፁሃን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በዞኑ ነዋሪዎች ድጋፍ መደረጉ ተገለፀ፡፡
የዞኑን ሰላም በማረጋገጥ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተቀናጀ ስራ መሰራቱ የተገለፀ ሲሆን ጥቃት አድራሾች ላይ እርምጃ መወሰዱም ተገልጿል፡፡
ጥቃቱ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት ያለመ መሆኑንም የዞኑ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡
በዞኑ የሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በጋብቻ ተሳስረው፣ ሀዘንና ደስታን እየተጋሩ መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
አሁን ላይ የዞኑ ነዋሪዎች ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሚገኙና ሁለቱ ህዝቦች በጋራ የገጠማቸውን ፈተና መመከት እንደሚገባቸውም አንስተዋል፡፡
እንደ ኦቢኤን ዘገባ የአካባቢው አባገዳዎች ለዓመታት ችግር የገጠማቸውን ወድሞቻችንን ተቀብለን አኑረናል ብለዋል፡፡
በእስካሁኑ አብሮነታችን ግን ይህንን አይነት ክስተት ገጥሞን አያውቅም በማለት ጥቃቱ ከደረሰ በኋላም ድጋፍ እያደረግንላቸው ነው ብለዋል፡፡
የባቦ ጋምቤል ወረዳ አስተዳደር የወረዳው ነዋሪዎች ተጎጂዎችን ለመደገፍ ያደረጉትን ጥረትም አድንቀዋል፡፡
የዞኑን ሰላም በማረጋገጥ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተቀናጀ ስራ መሰራቱ የተገለፀ ሲሆን ጥቃት አድራሾች ላይ እርምጃ መወሰዱም ነው ተጠቅሷል ፡፡