ምርጫ ነክ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለዐቃቤያነ ህግ ስልጠና እየተሰጠ ነው

ሚያዚያ 01/ 2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግና ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትብብር በየደረጃው ላሉ ዐቃቤያነ ህግ በምርጫ ነክ ጉዳዮች የክስ አቀራረብና የወንጀል ምርመራን አስመልክቶ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የህግ ቡድን መሪ አቶ ወንጌል አባተ፤ ስልጠናውን መስጠት ያስፈለገበት ዋና አላማም በምርጫ ህጉ ውስጥ አግባብነት ያላቸውን ቁልፍ ርእሰ ጉዳዮች ለማስገንዘብ እንዲሁም የአዋጁን አጠቃላይ ይዘት በማስተዋወቅ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን፣ የወንጀል አይነቶች፣ የስነ-ምግባር ጥሰትና መፍትኄዎችን በማመላከት ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና፣ ታአማኒነት ያለው የምርጫ ሂደት ለማከናወን የዐቃቤ ህጎችን ክህሎት ለማዳበር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ስር ስለተካተቱ ድንጋጌዎችና ዝርዝር የአፈጻጸም ሂደቶችን አስመልክቶ ወ/ሮ መነን አበበ መብራሪያ ሰጥተዋል። አዋጁ በአዲስ ከመጣ በኋላ የተካተቱ ነጥቦችን ጨምሮ ሎሎች ደምቦችም ምን እንደሚመስሉ ለቤቱ አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የንቃተ ህግ ትምርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዐቃቤ ህግ ዮሐንስ ግርማ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ሚዲያዎች፣ ታዛቢዎችና ሌሎች በምርጫው ሂደት የሚሳተፉ የምርጫ ስነ-ምግባርን በተከተለ መልኩ ስራቸውን ማከናወን እንደሚገባቸው ገልጸዋል ።
በመንግስት በኩልም ከምርጫ ምዝገባ ጀምሮ እስከ ማጠናቀቂያ ድረስ ያለውን ሂደት በተገቢውና ህጉ በሚፈቅደው አግባብ የሚከናወንበት ሁኔታ የተደላደለ በማድረግ ሰላማዊና ዲሞክራሳዊ ምርጫ የሚካሄድበት መንገድ ማመቻቸት ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የምርጫ መርህን ተከትሎ ምርጫ ማከናወን ግዴታ ነው ያሉት ዐቃቤ ህጉ ይህን ሳያደርጉ መቅረት ደግሞ የወንጀል ተጠያቂ እንደሚደርግ አብራርተዋል፡፡
በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር በላይሁን ይርጋ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ እንዲሁም የኢትዮጵያ የወንጀል ህግን አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የመምረጥና የመመረጥ መብት፣ የምርጫ ግጭት አፈታት ጋር ተያያዥነት ስላላቸው አለም አቀፍ መርሆች እና ተነጻጻሪ ልምዶች ላይ ማብራሪ አንደመሰጥ መግለጻቸውን ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያገኘነውን መረጃ ያመለክታል።