በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለመንግስት የሚሰጡ የሸኔ አባላት ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

መጋቢት 27/2016 (አዲስ ዋልታ) ባለፉት አራት ወራት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለመንግስት የሚሰጡ የሸኔ ቡድን አባላት ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል እና የፓርቲው የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

በኦሮሚያ ክልል በሸኔ ቡድን እንቅስቃሴ ቀዳሚ ተጎጂው ህብረተሰቡ ነው ያሉት ኃላፊው ህብረተሰቡ ቡድኑ ሲዘርፈው፣ ልጆቹን ሲገድልበት፣ የልማት ፕሮጀክቶችን ሲያወድም የቡድኑን ማንነት ተገንዝቦታል ብለዋል፡፡፡

ህብረተሰቡ አሁን ላይ የቡድኑን ማንነት መገንዘቡን ተከትሎ ከመንግስት ጎን በመቆሙ እና በመተባበሩ በተወሰደ የህግ ማስከበር እርምጃ የቡድኑ ፍላጎት መክሸፉንና የሀገር ደህንነት ስጋት እንዳይሆን ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

የፖለቲካ ፍላጎቱን ከጠመንጃ ውጪ ማስፈጸም ለሚሻ የትኛውም አካል መንግስት የሰላም በሩ ክፍት መሆኑን የገለጹት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚህም ባለፉት አራት ወራት በክልሉ እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚሰጡ የቡድኑ አባላት ቁጥር ጨምሯል ብለዋል፡፡

በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለመንግስት የሚሰጡ የቡድኑ አባላትም የተሀድሶ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ወደ ቀድሞ ስራቸው አንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡

የተከፈተውን የሰላም በር ወደ ጎን በመተው ፍላጎቱን በአፈሙዝ ማስፈጸም ለሚሻ አሸባሪ ቡድን መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በመስከረም ቸርነት