ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ሰላም አስከባሪ በመሆን ጭምር ሩዋንዳን ከችግር ለመታደግ አግዘዋል – ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ

መጋቢት 29/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወጣትነት ዘመናቸው በሰላም አስከባሪነት ተሰማርተው ሩዋንዳን ከችግር ለመታደግ አግዘዋል ሲሉ የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር በመሆን የሩዋንዳውያን የ”ኪዊቡካ 30″ ዓመት መታሰቢያ መርሐ ግብር ላይ ታድመዋል፡፡

መርኃ ግብሩ በሩዋንዳ የተፈጸመውን የዘር ጭፍጨፋ 30ኛ ዓመት የሚያስብ ሲሆን የአካባቢው አገራት መሪዎችም በመታሰቢያው ስነ-ስርዓት ላይ ታድመዋል፡፡

በመርኃ ግበሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ ሩዋንዳን በወቅቱ የገጠማትን ችግር ለመታደግ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እገዛ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።