በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው የእሳት ቃጠሎን መቆጣጠር ተቻለ


ሚያዝያ 14/2016 (አዲስ ዋልታ) በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር በተደረገ ርብርብ እሳቱ እንዳይዛመት መከላከል መቻሉን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የአግሮ ኢኮሎጂና የዱር እንስሳት ተመራማሪ ታደሰ ይግዛው እንደገለጹት የእሳት ቃጠሎው የተነሳው በፓርኩ ክልል አምባራስ በተባለው ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡

የእሳት ቃጠሎው የተነሳው ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ሲሆን ቃጠሎው በተነሳበት አካባቢ በጓሳ ሳርና ውጨና በተባሉ የፓርኩ የተፈጥሮ የደን ዛፎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡

በፓርኩ የዱር እንስሳት ላይ እስካሁን ቃጠሎው ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ ጠቁመው የቃጠሎው ምክንያት በውል አለመታወቁን ተናግረዋል።

የአካባቢው ሞቃታማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ለቃጠሎው መባባስ ምክንያት መሆኑን የገለጹት ተመራማሪው እሳቱ ያደረሰውን የጉዳት መጠን በዝርዝር ለማወቅ በቀጣይ ቀናት በሚቋቋም ግብረ ኃይል ጥናት ይደረጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ፓርኩ ውስጥ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡