ጀጎል የምስራቅ አፍሪካው አውራ ግንብ

ጀጎል ግንብ

#ሀገሬ

ሀገራችን ድንቅና ውብ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መስህቦች እንዲሁም ታሪካዊ ቅርሶችና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ናት። እነዚህ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች የውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ በመግዛት ይታወቃሉ። ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆን ባሻገርም የዓለም ቅርስ ሆነው የተመዘገቡ ብዙ ናቸው፡፡

ከእነዚህ የሀገራችን ውብ ቅርሶች በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል የሚገኘው የጀጎል ግንብ አንዱ ሲሆን የግንባታው መሀንዲሶች በወቅቱ የነበሩ አባቶች ናቸው። የጀጎል ግንብ የሀረሪ ህዝብ የኪነ ህንፃ ችሎታውን የሚያስመሰክር የታሪክ እና የጥበብ ውጤትም ነው፡፡

የሀረር ከተማ መለያና የዓለም ቅርስ የሆነው የጀጎል ግንብ የተገነባው በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ መሆኑን ታሪክ ያስረዳል።

ጀጎል በሀገር በቀል ዕውቅ የፈጠራ ባለቤቶች የተገነባ የሀገረሰብ ጥበብ ውጤት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በዘመኑ አባቶች ያለምንም ቴክኖሎጂ እገዛ ነበር ግንቡን ያበጃጁት። ከፋብሪካ ውጤቶች ነፃ የሆነና በአካባቢያቸው የሚገኘውን ጥሬ ዕቃ በመጠቀም የገነቡት የዚህ ግንብ ቆይታው ደግሞ የአባቶችን የጥበብ ከፍታን ያሳየ ነው። በዘመኑ በምስራቅ አፍሪካ በግንብ የታጠረች የመጀመሪያዋ ድንቅ ከተማ ሀረር እንደሆነች መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የግንባታው ዓላማም ከተማዋን ከጠላት ለመከላከል እንደሆነ ይነገራል፡፡

ግንቡ በ48 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን 5 በሮች አሉት፡፡ እነዚህ አምስቱ በሮች አምስቱን የእስልምናን አምድ የሚተርኩና የሚያብራሩ መሆናቸውም ይጠቀሳል፡፡

በሮቹ ወደተለያዩ መንደሮች መውጫና መግቢያ እንዲሁም ውሃ ያለበትን አቅጣጫ ለማመልከት የተሰሩ መሆናቸውም ይነገራል። እነዚህ በሮች የተለያየ መጠሪያ ያላቸው ሲሆን በአካባቢው አጠራር አስዲን በር፣ በድሮ በር፣ ሱክታት በር፣ ኤደር በር፣ አርጎ በር እና አሱሚ በር በሚል ስያሜ ይታወቃሉ።

በጀጎል ግንብ ውስጥ ከ2000 በላይ ጥንታዊና ባህላዊ ቤቶች ይገኙበታል። በግንቡ ውስጥ 356 መንገዶች ይገኛሉ፡፡ ከ90 በላይ መስጂዶችና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘ ሲሆን የመንግሥትና የግል ሙዚየሞችም በግንቡ ውስጥ ይገኙበታል፡፡ ግንቡ የዓለም ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው እ.ኤ.አ በ2006 ነው፡፡

የሠላም የፍቅርና የመቻቻል ተምሳለት የሆነችው የሀረር ከተማ ታይተው የማይጠገቡ የቱሪዝም መዳረሸዎች ያላት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት ሐረርን በማስዋብና በማስገጥ እንዲሁም ታሪክና ዝናዋን የማስቀጠል ዓላማ ይዞ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ የጀጎል ግንብ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ የተዋበና ድንቅ መስህብነቱን ይዞ ለትውልድ እንዲሻገር የማስዋብ የመንከባከብ ሥራዎች እየተካሄዱበት ነው፡፡

በግንቡ ውስጥ ያሉ መንገዶች ባህልና ታሪክን በሚያስተዋውቅና ቅርሶችን በሚያጎላ ሁኔታ በእጅ ጥበብ ውጤቶችም እያሸበረቁ ነው፡፡ ሀረርን ይጎብኙ ሀገርዎን ይወቁ፡፡
ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ