በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የብርቅዬ ዱር እንስሳት ቆጠራ ተጀመረ

ጥቅምት 18/2015 (ዋልታ) በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የብርቅዬ ዱር እንስሳት እና ብዝሃ-ህይወትን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያስችል የቆጠራ ስራ መጀመሩን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አበባው አዛናው እንደተናገሩት ቆጠራው የተጀመረው በፓርኩ ክልል ውስጥ በጥናት በተለዩ 68 የቆጠራ ቦታዎች ነው፡፡

በዚህ ሳምንት በተጀመረው የቆጠራ ስራ በ32 ቦታዎች የዋልያ ቆጠራ እንዲሁም በ36 ቦታዎች ደግሞ የቀይ ቀበሮዎች ቆጠራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በቆጠራ ስራው 150 የሚሆኑ የፓርኩ ሱፐርቫይዘሮችና ስካውቶችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ልምድና ሙያ ያላቸው አጋር አካላት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ቆጠራው በየዓመቱ ሲካሄድ የነበረ ቢሆንም በኮቪድና በአካባቢው በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት አለመካሄዱን የገለጹት ሃላፊው፤ የአሁኑ የቆጠራ ስራ ለአንድ ሳምንት እንደሚቆይ አስታውቀዋል፡፡

የቆጠራው ዋና አላማ የዱር እንስሳቱን አካባቢያዊ ስርጭት እንዲሁም የመኖሪያና የመመገቢያ ቦታዎች በመለየት አስፈላጊውን ጥበቃና ክብካቤ ለማድረግ እንዲቻል መሆኑንም ገልጸዋል።

ቆጠራው የዱር እንስሳቱን የእድሜና የጾታ ስብጥር ጨምሮ የጤናቸውን ሁኔታና የመዋለድ ምጣኔያቸውን በጥናት በተደገፈ መረጃ ለማደራጀት የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የቆጠራ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላም መረጃዎቹን በማደራጀትና በመተንተን ውጤቱን ለአጥኚዎች፣ ለተመራማሪዎችና ለጎብኚዎች ይፋ ይደረጋል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ለቆጠራ ስራው የሚያስፈልገውን ወጪ የተሸፈነው ከፓርኩ ጋር በቅንጅት በሚሰራው “አፍሪካን ዋይልድ ፋውንዴሽን” የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ድርጅቱ በፓርኩ ክልል በቱሪዝም ልማት፣ በአቅም ግንባታ፣ በፓርክ ማኔጅመንትና ስነ-ምህዳር ጥበቃ እንዲሁም በማህበረሰብ የቱሪዝም ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።

በዚህ ዓመትም ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው የፓርክ ልማትና ጥበቃ ስራዎች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መድቦ እየሰራ እንደሆነም ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ፓርኩ ከሁለት ዓመት በፊት አካሂዶት በነበረው የዱር እንስሳት ቆጠራ የዋልያ ብዛት ከ900 በላይ፤ የቀይ ቀበሮ ደግሞ 75 ያህል እንደሚሆን ማረጋገጥ ተችሎ እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

በፓርኩ ማንኛውም ዓይነት አደን የተከለከለና አስፈላጊው ጥበቃም የሚደረግለት መሆኑ ታውቋል።

በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት / ዩኔስኮ/ በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡