በሱዳን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የአፍሪካ ኅብረት ጥሪ

ጥቅምት 15/2014 (ዋልታ) በሱዳን የተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ እንዳሳሰበው የአፍሪካ ኅብረት አስታወቀ።
በሱዳን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ ኅብረቱ መግለጫ ውጥቷል፡፡
የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህመት በሱዳን ያለው አሁናዊ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳየው የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና ሌሎች የአገሪቱ ሲቪል ባለሥልጣናት መታሰራቸው ነው ሲሉ ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡
በሲቪሉ አስተዳደር እና በወታደሩ መካከል ያሉ ጉዳዮች በፖለቲካ ውይይትና እና ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ በፍጥነት እንዲፈታ ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አገሪቷን ለመታደግ እና ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ውይይትና መግባባት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነም በመግለጫቸው አስምረውበታል፡፡
ሊቀመንበሩ አክለውም የፖለቲካ መሪዎች ከእስር እንዲፈቱ እና ለሰብኣዊ መብት ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ከአፍሪካ ኅብረት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተያያዘ ዜና በሱዳን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
የሱዳን ጦር አዛዥና የሽግግር ምክር ቤቱ ሊቀ መንበር ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን አስታውቀዋል።
ወታደራዊ መኮንኑ በመግለጫቸው የሉአላዊ ምክር ቤት እና ሚኒስትሮች ምክር ቤት መፍረሱን፣ የክልሎች አሰተዳዳሪዎች እና ሌሎች አመራሮች ከሥልጣን መነሳታቸውን አስታውቀዋል።
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት፦
የአማርኛ ፌስቡክ ገፃችንን ይወዳጁ ይከተሉ
ከአረብኛ ፌስቡክ ገፃችን ጋርም ይጓዙ
የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
የትዊተር ገፃችንን ይከተሉ
አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!