በሲ ኤን ኤን ዘገባ የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን የዜጎች ምክር ቤት ተቃውሞ

መስከረም 5/2014 (ዋልታ) “በሲኤን ኤን ጣቢያ የሚስተናገዱ ዘገባዎች ሙያዊ መርህን ያከበሩና ትክክለኛ መሆን ይኖርባቸዋል” ሲል የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን የዜጎች ምክርቤት አሳሰበ።
ሲ ኤን ኤን ኢትዮጵያን በሚመለከት ላሰራጨው የተሳሳተ ዘገባ ምክርቤቱ ቅሬታውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን የዜጎች ምክርቤት ለሲ ኤን ኤን ዋና አዘጋጅ ሞርጋን ስቶቪያክ በላከው ደብዳቤ ጣቢያው ኢትዮጵያን በሚመለከት ሲያቀርባቸው የነበሩ ዘገባዎች የተዛቡና ወደ አንድ ወገን ያጋደሉ መሆናቸውን ገልጿል።
ከ750 ሺህ በላይ የሚሆኑ አባላትን በመወከል ደብዳቤውን ለጣቢያው ማስገባቱን የገለጸው ምክርቤቱ ጳጉሜ 4 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ወታደሮች ተገድለው ተከዜ ወንዝ ውስጥ ስለመጣላቸው “የአስከሬን ምርመራ ባለሙያዎች ማረጋገጫ ሰጥተውበታል” በሚል በቴሌቪዝንና በድረገጽ ያለ ተጨባጭ ማስረጃ ያቀረበው ዘገባ ቅሬታ ፈጥሯል ብሏል።
ዘገባው በግነትና በከባድ ቃላት የታጨቀና ድርጊቱም “የዘር ማጥፋት ነው” የሚል መልእክት እንዲያስተላልፍ ተፈልጎ መሰራቱን ያተተው ደበዳቤው፤ የህወሃትን የተሳሳተ መረጃ የማሰራጨት ፍላጎትን መሰረት ተደርጎ የተሰራው ዘገባ በበርካታ የጋዜጠኝነት መመዘኛዎች ህጸጾች ያሉት እንደነበር አንስቷል።
“የአሜሪካ ኮንግረስ የዘር ማጥፋት የሚል ቃል ባልተጠቀመበት ሁኔታ ዘገባው በዚህ መልክ መሰራት አልነበረበትም” ያለው ምክርቤቱ የህወሃትን የሰብአዊ መብቶች የመርገጥ ታሪክ ጣቢያው ይገነዘባል የሚል እምነት እንዳለውም ገልጿል።
ምክርቤቱ አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ላይ እያለ ሲፈጽማቸው ከነበሩት ግፎች በተጨማሪ ባለፈው አመት በማይካድራ በቅርቡም በአፋር ክልል ጋሊኮማ በአማራ ክልል በዳባት እና ጨና በተባሉ አካባቢዎች በርካታ ንጹሃንን በጅምላ መፍጀቱን አስታውሶ በደብረታቦርና ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎችም ባደረሰው ጥቃት በርካታ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት እንዲዘረፉና እንዲወድሙ አድርጓል ብሏል።
አሸባሪው ህወሃት ካለው ጨቋኝ የአገዛዝ ስርአት አኳያ ከነጻው ሚዲያ ጋር ተባብሮ ሊሰራ እንደማይችል ሊታወቅ እንደሚገባ አጽንኦት የሰጠው ምክርቤቱ፤ በአገሪቷ ፍትህ እንዲሰፍን ካስፈለገ በጣቢያው የሚስተናገዱ ዘገባዎች ሙያዊ መርህን ያከበሩና ትክክለኛ መሆን ይኖርባቸዋል ብሏል።
ከ30 አመታት በፊት በህወሃት አቀናባሪነት በደርግ ሰራዊት ተፈጽሟል የተባለውን አይነት ጭፍጨፋ ለማስፈጸምና ድርጊቱንም ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለማዋል ተደጋጋሚ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑንም ምክርቤቱ አንስቷል።