የአዲስ አበባ የአውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የነዳጅ ፍጆታውን በቴክኖሎጂ በማዘመኑ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉ ተገለፀ

ነሐሴ 16/2015 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የነዳጅ ፍጆታውን በውስጥ አቅም በበለጸገ የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ በማዘመኑ ባለፉት ሁለት ወራት ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የተጠቃሚውን እንግልት ለማስቀረት የትራንስፖርት ስምሪቱንና የተሽከርካሪ ጥገና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ እያዘመነ ነው።

በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺሕ 400 በላይ የሆኑ አውቶብሶች 36 በሚሆኑ ተቋማት የነዳጅ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሥምሪት ቁጥጥር ለማድረግ ከ850 በላይ አውቶብሶች ላይ አቅጣጫ ጠቋሚ (GPS) ሲም ካርድ እንደተገጠመላቸውም አብራርተዋል።

አቅጣጫ ጠቋሚው (GPS) በውስጥ አቅም በበለጸገው የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ መተግበሪያ አማካኝነት ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት መረጃ በማስተላለፍ የሥምሪት ቁጥጥር እያካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ግዛው ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት አውቶብሶች በተሟላ ቴክኖሎጂ የተደገፉ በመሆናቸው በድርጅቱ ባለሙያዎች በበለጸገው መተግበሪያ የቁጥጥር ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

ድርጅቱ በቴክኖሎጂ ተደግፎ በቀን አንድ ሺህ ያህል አውቶብሶችን በማሰማራት አንድ ሚሊዮን ሕዝብ እያጓጓዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈውን የቁጥጥር ስልቱን በማጠናከር በ2016 ዓ.ም በቀን አንድ አውቶብስ 12 ጊዜ ምልልስ እንዲያደርግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ድርጅቱ የተጠቃሚውን እንግልት ለማስቀረት የትራንስፖርት ስምሪቱንና የተሽከርካሪ ጥገና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ማዘመኑን አስታውቋል።

በድርጅቱ የቴክኒክና ግብዓት ዘርፍ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አዳነ አብደታ በበኩላቸው በመንግሥት የሚደጎሙ ከ1 ሺሕ 400 በላይ አውቶብሶች በተቋሙ የነዳጅ አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያገኛሉ።

የድርጅቱ ዋነኛ ወጪ የሆነው ነዳጅ፤ በመተግበሪያው ባካሄደው ቁጥጥር የነዳጅ ወጪን በመቀነስ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን ችሏል ብለዋል።

በቴክኖሎጂ ተደግፎ ሥምሪቱን ለመቆጣጠር እንዲያስችልም ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆነ አሰራር ተዘርግቶ ውጤታማ መሆን መቻሉ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

በመተግበሪያው አማካኝነት የጥገና አሰራር ሥርዓትን በመቆጣጠር ወደ መስመር የወጣ ተሽከርካሪ በአግባቡ የሚጠበቅበትን አገልግሎት እንዲሰጥ የሚቆጣጠርበት ሲስተም መሆኑን ገልጸዋል።

አውቶብሶቹ በቴክኒክ ብቁ እንዲሆኑ በየ15 ቀኑ በሚደረግላቸው የቴክኒክ ፍተሻ አደጋዎች እየቀነሰ መሆኑንም አመላክተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ተጠግነው የሚወጡ ተሽከርካሪዎች በመስመር ላይ በብቃት እየሰሩ ስለመሆኑ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸው የአውቶብሶችን ፍጥነትም በከተማዋ የፍጥነት ወሰን መገደቡንም ጠቁመዋል።

ከሚፈለገው ፍጥነት በላይ እና ሞባይል እያናገሩ የሚያሽከረክሩትን አሽከርካሪዎች ወደ ማዕከል ሪፖርት በሚያደርገው ሲስተም አማካኝነት ተቋሙ የእርምት እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም አስረድተዋል።