በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተከሰተ የመሬት መደርመስ አደጋ የእናት እና ልጅ ህይወታቸው አለፈ

መስከረም 25/2015 (ዋልታ) በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ጎተራ ወንጌላዊት ህንጻ ጀርባ ሌሊት 10:12 ሰዓት ላይ የመንገድ መደገፍያ ግንብ በመኖሪያ ቤቶች ላይ ተደርምሶ በቤታቸው ተኝተው የነበሩ የ35 ዓመት እናት እና የ7 ዓመት ልጇ ወዲያው ህይወታቸው አልፏል።

የድጋፍ ግንቡ መፍረሱን ተከትሎ የኮብልስቶን መንገዱም መሰረቱ ጭምር ተደርምሶ በቤቱ ላይ በማረፉ አደጋውን አባብሶታል ተብሏል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም የጸጥታ አባላት የሟቾችን አስከሬን ከፍርስራሽ  ውስጥ ማውጣታቸው ተገልጿል።

በቤቶቹ ውስጥ የነበሩ አራት ሌሎች ሰዎች ከአደጋው አምልጠው ራሳቸውን ማትረፍ መቻላቸው ተጠቅሷል።

በአደጋው ሶስት መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው ንጋቱ ማሞ ገልፀዋል።