የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ንግግሩ እንዲጀምር ጥሪ ማቅረቡን መንግስት አስታወቀ

> የአፍሪካ ኅብረት ግብዣ መንግሥት ከዚህ በፊት ያቀረባቸውን አቋሞች የጠበቀ ሆኖ ተገኝቷል

መስከረም 25/ 2015 (ዋልታ) – የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ንግግሩን የሚመሩ አካላትን፣ ቀንና ስፍራን አሳውቆ የሰላም ውይይቱ እንዲጀመር ኦፊሴላዊ ጥሪ ማቅረቡን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

“የአፍሪካ ኅብረት ግብዣ መንግሥት ከዚህ በፊት ያቀረባቸውን አቋሞች የጠበቀ ሆኖ ተገኝቷል። ንግግሩ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ብቻ እንዲሆንና ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲደረግ መንግሥት አቋሙን ሲገልጥ መቆየቱ”  አገልግሎቱ ዛሬ ባውጣው መግለጫ አስታውሷል።

“ግጭቱን ለመፍታት መንግሥት ሁሉንም ዓይነት የመፍትሔ ርምጃዎች ለመውሰድ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ይህንኑ አጠናከሮ የሚቀጥል ይሆናል” ብሏል።