በበልግ 965 ሺህ ሄክታር ለማልማት መታቀዱን የኦሮሚያ ክልል አስታወቀ

የካቲት 17፣ 2013 (ዋልታ) – በበልግ ወቅት 965 ሺህ ሄክታር ማሣ ለማልማት መታቀዱን 500 ሺህ ሄክታሩ በትራክተርና በበሬ ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን የኦሮሚያ ክልል አስታወቀ።

የበልጉ ሥራ ከመስኖ ልማት ጋር ተያይዞ እየተከናወነ መሆኑንም ገለጸ።

የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ በክልሉ የበልግ ምርት በሁለት ዙር እየተካሄደ ካለው መስኖ ልማት ጋር ተቀናጅቶ እየተከናወነ ነው።

ምስራቅና ምዕራብ ባሌ ፣ ምስራቅ ሀረርጌ፣ ጉጂ፣ምዕራብ ጎጂ እንዲሁም አርሲና ምዕራብ አርሲ ዞኖች አካባቢ በስፋት የበልግ አምራች እንደሆኑ የጠቀሱት ምክትል ኃላፊው ፣ በበልግ ምርት ዘመን 965 ሺህ ሄክታር ማሣ ለማልማት መታቀዱንና 500 ሺው ሄክታር ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል እንደ ኢፕድ ዘገባ ።

አሁን ያለው የዝናብ ሁኔታ ከተስተካከለና ዝናብ መጣል ከጀመረ በተለይም ምስራቅና ምዕራብ ባሌ ቀጥታ ማሳውን በዘር ወደ መሸፈን እንደሚገቡ ጠቁመዋል።