በቡድን 7 አባል ሃገራት የወጣው ትግራይ ክልልን የተመለከተ መግለጫ ከእውነታ የራቀ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 26/2013 (ዋልታ) – የትግራይ ክልልን አስመልክቶ በቡድን  ሰባት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የወጣው መግለጫ እውነታውን ያላገናዘበ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የ G7 አባል ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትግራይ ክልል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ መንግስት በክልሉ የተከሰተውን ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አመላክቷል፡፡

መንግስት የሚዲያ ተቋማትን ጭምሮ ለሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለተገደብ እንቅስቃሴ ፈቃድ ቢሰጥም ከአለም አቀፉ ማሕበረሰብ እየቀረበ ያለው እርዳታ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

በክልሉ ተፈጽሟል ስለተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትም አለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ምርመራ እነዲያደርጉ ፈቃድ የተሰጣቸው ሲሆን ሥራቸውን በቅርቡ እንደሚጀምሩ  ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስፍሯል፡፡

እንዲሁም መንግስት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ተረጂዎች እርዳታ ማቅረቡን ያስታወሰው መግለጫው ከዚህ ውስጥ ከአለም አቀፍ ማሕበረሰብ የተገኘው የዕርዳት መጠን ከአንድ ሶስተኛ በታች መሆኑን ገልጿል፡፡

በመሆኑም በክልሉ ያለው ችግር ሙሉ በሙሉና በወቅቱ እንዲቀረፍ ከተፈለገ በቂ የእርዳታ አቅርቦትን ማሰባሰበ ላይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በድንበር አካባቢ የነበሩ የኤርትራ ወታደሮች አሁን ለቀው  መውጣት የጀመሩ መሆኑን እና አካባቢው በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንዲያዝ እየተደረገ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል፡፡