በቤተክርስቲያንቱ አባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በውይይት መፈታቱ ተገለጸ

የካቲት 8/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በውይይት መፈታቱ ተገለጸ፡፡

በቤተክርስቲያኒቱ የገጠመውን ፈተና ለመፍታት የሁለቱ ወገኖች የሐይማኖት አባቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ ምክክር አድርገዋል፡፡

አንድነትን የሚያጸና እና አገልግሎትን የሚያሰፋ መንገድ መከተል ተገቢ መሆኑን በማመን ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የሐይማኖት አባቶች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ከቋንቋ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቤተ ክርስቲያን የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል ከመግባባት ላይ መደረሱ ተመላክቷል። ለዚህም በጀትና የሰው ኃይል ማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራል ነው የተባለው፡፡

በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ እምነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ማሰልጠኛ ኮሌጅ እና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲጠናከሩ እና ቤተ እምነትን ለትውልድ ለማሻገር መፈታት የሚገባቸውን ችግሮች በጥናት እና በአሠራር መፍታት እንደሚገባ መተማመን ተፈጥሯልም ነው የተባለው፡፡