አፍሪካ የጤና እና የምግብ ችግሯን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነች ነው- ሙሳ ፋኪ ማሃማት

ሙሳ ፋኪ ማሃማት

የካቲት 8/2015 (ዋልታ) አፍሪካ የጤና እና የምግብ ችግሯን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ገለጹ።

42ኛው የአፍሪካ ሕብረት የአስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ተጀምሯል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት አፍሪካ በቱርክዬ እና ሶርያ በደረሰው ተፈጥሯዊ አደጋ ሀዘናቸውን በመግለፅ ስብሰባውን አስጀምረዋል።

ሊቀ-መንበሩ አፍሪካ ጤና እና ስነ-ምግብ ቁልፍ የሕብረቱ ስራዎች አድርጋ በቀዳሚነት እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።

የአፍሪካ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል እና የአፍሪካ መድሀኒት ኤጀንሲ መቋቋማቸው ይህን ጥረቷን ለማሳካት ብሎም ከጥገኝነት ለመላቀቅ እንደሚያስችላት ጠቅሰው በጤና አጠባበቅ እና በስነ-ምግብ ራስን ለመቻልም አገራት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ በኩል አፍሪካ የንግድ ግብይት ለማሳለጥ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራም ለማፋጠን እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣ ያላትን ሃብቶች አሟጣ ለመጠቀም፣ ዲጂታላይዜሽንን ለማፋጠን፣ የዕውቀት ሽግግር ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

በአህጉራዊ ሰላምና ደህንነት በኩል ደግሞ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ የመፍታት ማዕቀፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት በሕብረቱ መሪነት ሰላም የማረጋገጥ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የውጭ ጣልቃገብነት ለችግሮቹ መባባስ እንጂ መፍትሔ እንደማይሆን ገልፀው፣ በሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በሊቢያ፣ በጊኒ ቢሳው፣ በሶማሊያ፣ በማሊ፣ በቡርኪናፋሶ የተከሰቱ የሰላም ችግሮች እንዲፈቱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን በድርድርና በሌሎች አማራጮች ወሳኝ ሚና ስለመጫወቱ አንስተዋል።

ሊቀመንበሩ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፍትሔ በሚለው መርህ አህጉራዊ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈቱ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ህብረት ጥረቶችን አባላቱና አጋር አገራት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በወጣቶችና ሴቶች ፋይናንስ አካታችነት ረገድ በተለይም የ2063 የአፍሪካ አጀንዳ ዕውን ለማድረግ በሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ተለዋጭ በሆነው ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካ አፍሪካ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ የባለብዙ ወገን ትብብሮችን እንደምታጠናክር መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ምክር ቤቱ በ45ኛው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች መደበኛ ስብሰባ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል።

ለአብነትም በሕብረቱና ተጠሪ ተቋማቱ ዓመታዊ ሪፖርት፣ የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ ማቋቋም ሂደት፣ የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ስራ ማስጀመር ሪፖርት፣ የ2022 የአፍሪካ ስነ-ምግብ ፍኖተ ካርታ ሪፖርት ያደምጣል።

እንዲሁም የ2013 የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ማፋጠን መሪ ቃልን የማፅደቅ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ምርጫ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ሕብረት ስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት የአባል አገራትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ያቀፈ ነው።