በብሄር ሳንለያይ የአከባቢያችንን ሰላም እንጠብቃለን- የማንዱራ ወረዳ ነዋሪዎች

የካቲት 26/2013 (ዋልታ) – በብሔር ሳንለያይ የአካባቢያችንን ሰላም እንጠብቃለን ሲሉ በመተከል ዞን የማንዱራ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ከማንዱራ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በወረዳው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ ሌተናል ጄኔራል አስራት በወረዳው ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች ከህዝብ ጋር በመቀናጀት በተሰራ ስራ አንፃራዊ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

የታየው ሰላም የአካባቢው ነዋሪዎች አንድነታቸውን አስጠብቀው በሰሩት ውጤታማ ስራ መሆኑንም ገልጸዋል።

“የእኛ ህዝብ እርስ በእርሱ የተጋባ፣ የተዋለደ እና በማህበራዊ ህይወት የተሳሰረ ስለሆነ ሰላም እና አንድነትን አስጠብቆ በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅሞ መልማት ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ

የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከሁሉም ማህበረሰቦች የተውጣጡ ሚልሻዎች ተመልምለው ሥልጠና እየተሰጣቸው እንደሆነም አስታውቀዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ የማንዱራ ነዋሪዎች እርስ እርስ የተጋቡ፣ የተዋለዱ እና በማህበራዊ ህይወት የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢያችን እየታየ ያለው የጸጥታ ችግር የፀረ ሰላም ሃይሎች የፈጠሩት እንጂ የማህበረሰቡ አይደለም ብለዋል።

ይህን ችግር በአጭር ጊዜ ማጥፋት የሚቻለው በቅንጅት ስሰራ መሆኑን ገልጸው “ሰላም ለሁሉም ማህበረሰብ መስፈን አለበት” ብለዋል።

ከሁሉም ማህበረሰብ ከተመለመሉት ሚልሻዎች ጋር ተባብሮ በመስራት አካባቢያቸውን ከፀረ ሰላም ሃይሎች እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በመተከል ዞን የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል በዞኑ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል።