ዩኔስኮ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የማህበረሰብ ሬዲዮ አቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ

ኅዳር 21/2015 (ዋልታ) ዩኔስኮ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራና የማህበረሰብ ሬዲዮ አቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ካለው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ጎን ለጎን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከዩኔስኮ የተግባቦትና መረጃ ረዳት ዳይሬክተር ቶፊቅ ጀላሲ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራ እና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የወደሙ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢዎችን መልሶ የመገንባት ስራን ዩኔስኮ እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

በተለይ የማህበረሰብ ሬዲዮዎቹ በጦርነቱ ምክንያት የስነ-ልቦና ጫና የደረሰባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ለማገዝ ትልቅ ጠቀሜታ ስላላቸው ድጋሚ የመጠገንና የአቅም ግንባታ ስራ ያስፈልጋዋቸል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የዩኔስኮ የተግባቦትና መረጃ ረዳት ዳይሬክተሩ በበኩላቸው ዩኔስኮ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራና የማህበረሰብ ሬዲዮ መጠገንና አቅም ግንባታ ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።