በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ስራን በተመለከተ የተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች የተሳኩ ናቸው – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

መንግስት በትግራይ ክልል ሲያደርግ የነበረውን የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ በድል መጠናቀቁን አስመልክቶ የተሰሩ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች የተሳኩ ስለመሆናቸው አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ በትግራይ የተከናወኑ ህግን የማስከበር ዘመቻዎችን ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስራ ሰለመሰራቱ ጠቅሰው፣ ህግ የማስከበር ዘመቻው በመጠናቀቁ ከዚህ በኋላ ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ ስራው እየተከናወነ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
በተለይም ህግ የማስከበር ስራውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮነንን ከተለያዩ የአፍሪካ እና የአውሮፓ አገራት እንዲሁም ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ውይይት ተደርጎ ስላለው ነባራዊ ሁኔታም ገለፃ ስለመደረጉ አብራርተዋል፡፡
ህግ የማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ ከአካባቢው ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችንም የመመለስ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ያነሱት ቃል አቀባዩ፣ በክልሉ በተለያዩ ዘርፉ ከተሰማሩ ኢንቨስተሮችም ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው ወደ ስራ እንዲገቡ ዝግጅት ስለመጀመሩም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
(በሕይወት አክሊሉ)