ግንቦት 09/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል ውስጥ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ልዩ ትኩረት በመስጠት በዘር ወቅት የሚያስፈልጉ የግብርና ግብዓቶች በበቂ መጠን እየቀረቡ መሆኑ ተገለጸ።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተስፋ እንደገለጹት፣ ክልሉ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የግብርናውን ሥራ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው።
በተለይም አርሶ አደሩ በዘር ወቅት የሚያስፈልገውን የአፈር ማዳበሪያ መቶ በመቶ ግዢው ተጠናቅቆ ለክልሉ ተደራሽ ሆኗል።
የትግራይ ክልልን ጨምሮ በሀገሪቱ በሚገኙ በሁሉም ክልሎች የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱና በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ በተያዘው በጀት ዓመት ከሁሉም ክልሎች በተሰበሰበው ፍላጎት 18 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ማወቅ ተችሏል ብለዋል።
ከዚህም ውስጥ ትግራይ ክልል 800 ሺህ ኩንታል ያስፈልገኛል ብሎ ባቀረበው ፍላጎት መሠረት በልዩ ሁኔታ መቶ በመቶ እንዲቀርብ ሆኗል።
በ2012 ዓ.ም ወደ ክልሉ ገብቶ ጥቅም ላይ ያልዋለ 214 ሺህ 867 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ በተያዘው በጀት ዓመት ከተገዛው ደግሞ 225 ሺህ 325 ኩንታል በድምሩ 440 ሺህ 169 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለክልሉ የቀረበ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።