በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው ሠብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ኮሚሽኑ ገለጸ

በትግራይ ክልልና በሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች ለዜጎች የሚደረገው ሠብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለፀ።

በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ክስተቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ አስከትለዋል፡፡

በዚህ ሳቢያ ሠብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ቁጥር በመጨመሩ የመንግስትን የምላሽ አሰጣጥ ተግባር ፈታኝ አደርጎታል፡፡

በቅርቡ በትግራይ ክልል የተፈጸመውን ሕገወጥ ተግባር ተከትሎ መንግስት ሕግ ለማስከበር በወሰደው እርምጃ ሽንፈት የተከናነበው የጥፋት ቡድን ያደረሰው የመሰረተ ልማት ውድመት በርካታ ዜጎችን ሠብዓዊ ድጋፍ ፈላጊ አድርጓል፡፡

ዘመቻውን ተከትሎ መንግስት በተቆጣጠራቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች ሠብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ ሲሆን መንግስትም ድጋፍ ለሚያሻቸው ዜጎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በአገሪቷ ሠብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን እንደሚጠጋና ከዚሁ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮኑ በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳመና ዳሮታ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ድጋፍ ከሚሹት መካከል ለ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የኅብረተሰብ ክፍሎች ሠብዓዊ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።

በክልሉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸው ሠብዓዊ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ ተፅእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና ክፍተቱን ለመሙላት ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት በመስራት ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ዳመና የሰው ሕይወት ለመታደግና ለተጎጂዎች በአፋጣኝ ድጋፍ እንዲደርስ ከአካባቢ ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት እንዲከፋፈል ኮሚሽኑ በትጋት እየሰራ እንደሚገኝና በቀጣይም ሁሉንም አካባቢ የማድረሱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከቁጥር ይልቅ ለተጎጂዎች በቅድሚያ ሠብዓዊ ድጋፍ ማድረስ ላይ ትኩረት አደርጎ እየሰራ መሆኑን ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ሰብዓዊ ድጋፋን መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ እንዲሁ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ዳመና 200 ሺህ ኩንታል የሚሆን የምግብ አቅርቦት ከጅቡቲ ወደብ ወደ መቀሌ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከኮሚሽኑ በተጨማሪ የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅት 100 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የምግብ ፍጆታ አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል ለማጓጓዝ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳሉት እስካሁን በክልሉ ጉዳት ለደረሰባቸው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች 220 ሺህ ኩንታል የምግብ ፍጆታ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡