የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 95ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምከር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባቸውን የመንግስት የልማት ድርጅቶች የዕዳ ጫና ለማቃለል የቀረበ የውሳኔ ሃሳብ እንዲሁም የእዳ እና የሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው::

በአገሪቱ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና መሠረተ ሰፊ የሆነ የልማት እንቅስቃሴ እንዲኖር ታስቦ ከዓመታት በፊት ተጀምረው ከነበሩት በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ በቂ ዝግጅት ሳይደረግባቸው የተጀመሩ፣ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግር የታየባቸው፣ ብቃት ባለው እመራር ያልተመሩ እና ሌሎችም የፕሮጀክት አስተዳደር ከህሎት ከፍተት የሚታይባቸው ናቸው።

በመሆኑ የሜጋ ፕሮጀክቶች ባለቤት የሆኑት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር በብድር የወሰዱትን ገንዘብ መከፈል እልቻሉም፡፡

አገራችን ከገጠማት የኢኮኖሚ ስብራት እንዱ ክፍል ነበሩ፡፡

የአገር በቀል ኢኮኖሚ ልማት ማዕቀፍ ታሳቢ ያደረገ የማሻሻያ ትግበራ አካል ተደርገው ተወስደዋል፡፡

በዚህም መነሻነት የልማት ድርጅቶቹን የእዳ ጫና ለማቃለል እና ውጤታማ ሆነው እንዲዘልቁ ለማስቻል በቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምከር ቤቱ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል አጽድቋል፡፡

በተጨማሪም ተለይተው የሚሰጡትን የልማት ድርጅቶች እዳዎች የሚያስተዳድር እንዲሁም በጥናት በተለዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰማራ ብሎም ውጤታማ የእዳና ሃብት እስተዳደር ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ተወያይቶ በማጽደቅበነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

  1. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተደረገ ለሴቶች ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በሴቶች ባለቤትነት የሚካሄዱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በስልጠናና በፋይናንስ ለመደገፍ፣ ኢንተርፕራይዞች እንዲበራከቱ እና ወደተሻለ ደረጃ እንዲያድጉ ለማድረግ፣ እንዲሁም ሴቶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እናለስራ እድል ፈጠራ ያለውእስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡

ስምምነቱም የ100ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ሲሆን፣ ከወለድ ነጻ፣ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያለው፣ በ38 ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅና ከአገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም መሆኑን በማረጋገጥ የብድር ስምምነት ማጽደቂያ አዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

በተጨማሪም መቀመጫው በፊላንድ ከሆነው ዳንስኬ ባንክ ጋር የተደረገ ለሜቲዎሮሎጂ ምልከታ መሰረተ ልማት እና የትንበያ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ምከር ቤቱ ተወያይቷል፡፡

የስምምነቱ አላማም ለብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዘመናዊ የሆኑ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳሮች፣ የመብረቅ መከታተያና ተንቀሳቃሽ የአየር ብክለት መከታተያ ጣቢያዎችን ማቋቋሚያ እና የሰው ኃይል እቅም ግንባታ የሚውል ነው፡፡

ብድሩም 8.8 ሚሊየን ዩሮ ሲሆን ወለዱ፣ የብድር ማስተዳደሪያ እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች በፊንላንድ መንግስት የሚሸፈኑ ሆነው የአምስት አመት የችሮታ ጊዜ ያለው በ15 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ እና ከአገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂጋር የሚጣጣም መሆኑን በማረጋገጥ ስምምነቱይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

በመጨረሻም ምከር ቤቱ የፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ እሰጣጥ እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።

በስራ ላይ ያሉት የጥብቅና አዋጅ ሀገሪቱ ካለችበት አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንጻር ሊኖራት የሚያስፈልጉ የጥብቅና አገልግሎቶችን በተደራጀ ሁኔታ የሚመራ አለመሆኑ፤ ከጠበቆች ዲሲፕሊን ክስ እና ቅጣት አንጻር ይርጋ፣ ደጋጋሚ ጥፋተኝነትን፣ ከቅጣት በኋላ ስለሚኖር መሰየም እና ተያያዥ ጉዳዮች ምላሽ የማይሰጥ በመሆኑ፤ የጥብቅና ስራ በግለሰብ ደረጃ እንጂ በንግድ ተቋም ደረጃ እንዲሰራ የማይፈቅድ በመሆኑ የአዋጁን ማሻሻያ እስፈላጊ አድርጎታል፡፡

ከዚህ አንጻር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ሀገሪቷ እያካሄደች ያለችውን ዘርፈ ብዙ ሪፎርም ታሳቢ ባደረገ እና አለም አቀፍ ተሞከሮዎችን ባገናዘበ መልኩ የተዘጋጀ ነው፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡