በትግራይ ደቡባዊ ዞን የተማሪዎች ምዝገባ ተጀመረ

ግንቦት 13/2013(ዋልታ) – በትግራይ ደቡባዊ ዞን ትምህርት ለማስጀመር የተማሪዎች ምዝገባ መጀመሩን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የዞኑ ማህበራዊ ጉዳይ መመሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው አስተባባሪ አቶ አብርሃ ደሳለው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተማሪዎች ምዝገባ የተጀመረው በሁለተኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነው።
ምዝገባው ከተጀመረባቸው የዞኑ አካባቢዎች መካከል መኾኒ እና አዲሸሁ ከተሞች እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ ምዝገባውን በማጠናቀቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትምህርት እንደሚጀመር ገልጸዋል።
ተማሪዎች ትምህርት በሚጀምሩበት ወቅት ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ 40 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፤ እንዲሁም ሳኒታይዘር ዝግጁ ተደርጓል ብለዋል።
በማይጨውና ሌሎች የዞኑ አካባቢዎች የተማሪዎች ምዝገባ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አቶ አብርሃ ጠቁመዋል።