የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ የተላለፉ ከ1ሺህ በላይ ተሸከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል – የትራንስፖርት ቢሮ

ግንቦት 13/2013(ዋልታ) – የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ በተላለፉ 1ሺህ 2 ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡
ከግንቦት 2 እስከ 10/2013 ዓ.ም ብቻ ትርፍ በመጫን 603፣ ማስክ አለማድረግ 204፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል 91፣ መስመር አለመሸፈን 65፣ ታፔላ አለመስቀል 38 እና በስራ ሰዓት መቆም 1 በድምሩ 1ሺህ 2 ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል፡፡
በሚያዝያና መጋቢት ወር 10 ሺህ 305 ተሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን 4 ሚሊዮን 609 ሺህ ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል፡፡
ትርፍ መጫን፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ የኮቪድ 19 መከላከያ ተግባራት አለማከናወን፣ በስራ ሰዓት ያለ ሥራ ቆሞ መገኘት እና ታፔላ ሳይሰቅል መስራት ከ5 መቶ እስከ 2 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በመመሪያው ተደንግጓል፡፡
ከባድ ተሽከርካሪዎች የተፈቀደላቸውን ሰዓት ሳያከብሩ ከተገኙ 5 ሺህ ብር ቅጣት ያስቀጣል፡፡
መመሪያው ከወጣበት ከሚያዝያ 26/2013 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የንቅናቄ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት በዋና ዋና ተርሚናሎች እና መስመሮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡