በኅዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ጉዳይ ምክክር

መስከረም 5/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻቸው ክርስቶፌ ሉቱንዱላ ጋር ተወያዩ፡፡
ውይይታቸውም በአፍሪካ ኅብረት አስተባበሪነት የሚካሄደውን የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነው ተብሏል፡፡
በወቅቱም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ በግድቡ የድርድር ሂደት የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት ለተጫወተው የመሪነት ሚና አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ድርድሩ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝት ገልጸው ይህም በሁሉም አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ላይ መድረስ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ በኩል በማንኛውም ጊዜ በድርድሩ ለመሳተፍ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠውላቸዋል፡፡
ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲሰፍን በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ጽኑ ፍላጎትም አስታውሰው ናይል የተፋሰሱ አገራት የትብብር እንጂ የግጭት መንስዔ መሆን እንደማይገባውም ተናግረዋል፡፡
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፌ ሉቱንዱላ በበኩላቸው፣ ድርድሩ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ላሳየችው ቁርጠኝት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
አገራቸው ለአፍሪካዊ ችግሮች የአፍሪካዊ መፍትሔ መርህን አጥብቃ የምታምን መሆኗን ስለማረጋገጣቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡