በኒው ደልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ 125ኛውን የአድዋ የድል በዓል አከበረ

የካቲት 24/2013 (ዋልታ) – በህንድ ኒው ደልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በህንድ ማርዋ ዲ ዩኒቨርሲቲ ከሚማሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን 125ኛውን የአድዋ የድል በዓል አከበረ።

ትናንት በተከበረው የአድዋ የድል በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ዶክተር ትዝታ ሙሉጌታ የአድዋ ድል ውጤት የተገኘው ቀደምት አባቶችና እናቶች ለነጻነት ባላቸው ቀናኢነት እንደሆነ ገልጸዋል።

ድሉ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች የነጻነት መንገድ የከፈተ ታላቅ ድል መሆኑን አስታውሰዋል።

አድዋ ለዛሬው ትውልድ በትብብር በመስራት የጋራ ግቡን ለማሳካት መነቃቃትን የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል።

የአድዋ ድል መከበር የአፍሪካን አንድነት ማጠናከር ከሚቻልባቸው ወሳኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሆነም አምባሳደሯ አመልክተዋል።

በበዓል አከባበሩ ላይ የተገኙት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የተለያዩ የባህል ትርዒቶችን ያቀረቡ ሲሆን አድዋን የሚዘክሩ ትረካዎችና ቲያትር አቅርበዋል።

የማርዋ ዲ ዩኒቨርሲቲ ሃላፊዎች፣ የአፍሪካ አገሮች ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በድል በዓል አከባበሩ ላይ እንደታደሙ ከኤምባሲው የተገኘ መረጃ ያሳያል።