በአማራ እና አፋር ክልሎች የተሰማሩ ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድኖች

መስከረም 19/2014 (ዋልታ) ከሰብዓዊ አጋሮች ጋር በቅንጅት ከ50 በላይ ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድኖች ተቋቁመው በአማራ እና አፋር ክልሎች መሰማራታቸውን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የብሄራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በአማራ እና አፋር ክልሎች በተቋቋሙት የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ሰጭ ማዕከላት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ አፈጻጸማቸው ተገምግሟል፡፡

በክልሎቹ ልዩ ትኩረት የሚሹ ቦታዎች ላይ እየተከናወኑ ያሉ የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት፣ የመሰረታዊ ጤና፣ ውሃና የንጽህና አገልግሎቶች አቅርቦት እንዲሁም ለህጻናት፣ እናቶች እና አረጋውያን አልሚ ምግብ አቅርቦት ላይ እየተደረገ ያለው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ያሳዬ ሲሆን በቀጣይም የስርጭት ፍትሀዊነትና ተደራሽነት፣ ውጤታማ ቅንጅታዊ ስራ፣ ፆታዊ ጥቃት ለተፈፀመባቸው ሴቶች የማገገሚያ ማዕከላትን ማጠናከር እና ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተደረገ ያለው ክትትል የበለጠ እንዲሻሻል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በመጠለያዎች የሚገኙ ዜጎችን ከመደገፍ ጎን ለጎን ቤት ለቤት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን ለመድረስ የተጀመረው ስራም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በአሸባሪው ሀይል የወደሙ ተቋማትን በጊዜያዊነት የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ ተጀምሯል፡፡

በተቋማት እየተሰጡ ካሉ የጤና አገልግሎቶች በተጨማሪ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከሰብዓዊ አጋሮች ጋር በቅንጅት ከ50 በላይ ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድኖች ተቋቁመው በሁለቱ ክልሎች ተሰማርተዋል፡፡

ወደ ትግራይ ክልል ገብተው ያልተመለሱ የጭነት መኪኖች ጉዳይ የቅርብ ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የበረሃ አንበጣ በመከሰቱ የኬሚካል እና መርጫ መሳሪያ አቅርቦት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በጥቃት የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን የመጠገንና መልሶ ግንባታና ማቋቋም ተግባራት በተለይም በጤና ተቋማት እና መንገዶች መጀመሩን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡