በአማራ ክልል የገና በዓል በሰላም መጠናቀቁን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ

ታኅሣሥ 29/2014 (ዋልታ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በሮሀ ቅዱስ ላሊበላ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በክልሉ በሁሉም ቦታዎች በሰላም መከበሩን የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ተናገሩ።

ኃላፊው በሮሀ ቅዱስ ላሊበላ ቤተ ክርስቲያን በሰጡት መግለጫ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሰላም ተከብሯል ነው ያሉት።

በክልሉ በሁሉም ቦታዎች ሃይማኖቱና ባህሉ በሚፈቅደው መሰረት በሰላምና በአንድነት ማክበር ተችሏል ያሉት ኃላፊው ከ10 ቀናት በኋላ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል በድምቀት ለማክበር ስንቅ የሚሆን ዝግጅትም በዓልም ነበር ሲሉ ገልፀዋል።

በላሊበላ እና በመላ አማራ ክልል የገና በዓል በሰላም እንዲከበር ያደረጉ የፀጥታ ኃይሎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ለኅብረተሰብ ምስጋና አቅርበዋል።

በምንይሉ ደሰይበለው (ከላሊበላ)