ከ90 ሺህ በላይ ሃሰተኛ ብር በቁጥጥር ስር ዋለ


ጳጉሜን 1/2015 (አዲስ ዋልታ) በአራዳ ክፍለ ከተማ አንዱን ባለሁለት መቶ ሀሰተኛ የብር ኖት በ80 ትክክለኛ ብር ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ግለሰቦች እጅ ከ 90 ሺህ በላይ ሃሰተኛ ብር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ገለጸ፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከሃሰተኛ የገንዘብ ዝውውር ጋር ተያይዞ በደረሰው ጥቆማ እና ባደረገው ክትትል በዚህ ወንጀል ተሳትፎ አላቸው የተባሉ 3 ግለሰቦችን ከቦሌ እና ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አሳውቋል፡፡

97 ሺህ 400 ሀሰተኛ ብር ከተጠርጣሪዎቹ እጅ የተያዘ ሲሆን በደላላ አማካይነት አንዱን ባለሁለት መቶ ሀሰተኛ የብር ኖት በ80 ትክክለኛ የኢትዮጵያ ብር ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ እንደነበረም ታውቋል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የተጀመረው ምርመራ ተጠናክሮ እንደሚቀጠልም ነው ፖሊስ የገለጸው፡፡

በዓላት በሚቃረቡበት ወቅት ሃሰተኛ ገንዘቦችን ወደ ገበያው በማሰራጨት በህገ ወጥ መንገድ ጥቅም ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች መኖራቸውን ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ አስታውሷል፡፡

ህብረተሰቡ ለበዓል በሚያደርገው ግብይት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ ፖሊስ ማሳሰቡን ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡