በአርባ ምንጭ ከተማ ብልጽግና ፓርቲን የሚደግፍና የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሄደ

ሰኔ 06/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ክልላዊ መንግስት ጋሞ ዞን ብልጽግና ፓርቲን የሚደግፍና በሃገር ሉዋላዊነት ላይ የሚቃጣን የውጪ ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ ሰልፍ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ህብረተሰቡ ለብልጽግና ፓርቲ እያደረገ ላለው የድጋፍ ሰልፍ አመስግነዋል፡፡
በክልል ደረጃ ብልጽግና ሲያካሂዳቸው የነበሩ የምርጫ ቅስቀሳ ስራዎች በስኬት በመጠቃለል ላይ ናቸው ያሉት የደቡብ ክልል ብልጽግና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ሕዝቡ ምርጫውን ለማደናቀፍና በሂደቱ ሁከትና ብጥብጥ ለፍጠር የሚጥሩ ፀረ ሰላም ሃይሎችን እንቅስቃሴ በንቃት መከታተል ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ሕዝባዊ ድጋፉ መነሻ በብልጽግና አመራር ባለፉት ጥቂት አመታት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና በማረጋገጥ ላይም የሚገኙ የልማት፤ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጅማሮዎች ናቸው ያሉት ደግሞ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ናቸው፡፡
ሕብረተሰቡ በምርጫ ወቅትም ሆነ ከምርጫ በኋላ ሊነሱ ከሚችሉ አፍራሽ ተግባራትና የተዛቡ መረጃዎች እራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡
በድጋፍ ሰልፉ የተሳተፉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
መረጃው የተገኘው ከዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው፡፡