በአዲስ አበባ ከሚያዚያ 16 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መንገዶች ብቻ እንደሚፈጸም ተገለጸ

መጋቢት 29/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚያዚያ 16 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መንገዶች ብቻ እንደሚፈጸም የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መንገዶች ብቻ የሚፈፀምበትን የድርጊት መርኃ ግብር በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ተወያይቷል።

የውይይቱ ዓላማ በመዲናዋ የሚገኙ ሁሉም የነዳጅ ማደያዎችና ኩባንያዎች በአሰራሩ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲይዙ ለማስቻል መሆኑ ተነግሯል።

በወቅቱ የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ ባለስልጣኑ የነዳጅ ግብይትን በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም ቀደም ብሎ ከነዳጅ ማደያና አከፋፋይ ኩባንያዎች ጋር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው አሁን ደግሞ ለሙሉ ትግበራው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓቱ በአማራጭነት ለሙከራ እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው ከሚያዚያ 16 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በአስገዳጅ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መንገዶች ብቻ እንደሚፈጸም ተናግረዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ማንኛውም የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ ብቻ የሚፈጸም መሆኑን ተገንዝቦ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አተገባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ በአስገዳጅነት እንደሚተገበርም ጠቁመዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሞባይል መኒ ኦፊሰር ብሩክ አድሃነ የነዳጅ ግብይትን በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መንገዶች በማድረግ ረገድ በቴሌ ብር ውጤታማ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አንስተው ለዚህም ባለፉት ዘጠኝ የሙከራ ወራት በቴሌ ብር ብቻ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ግብይት መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

የነዳጅ ግብይቱን በአግባቡ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መንገዶች ለማከናወን የሚያስችል ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መገንባቱንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ ማደያዎች ማኅበር አባል ሚካኤል ገብረስላሴ እና የማህበሩ የቦርድ አባል ኤፍሬም ተስፋዬ የነዳጅ ግብይት ስርዓቱ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መንገዶች ብቻ መሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

በተለይ ለነዳጅ አዳዮች ጥሬ ገንዘብ በመቁጠር የሚያባክኑትን ጊዜ ከመቅረፍ አንፃር እንዲሁም በማደያዎች የሚቀመጥ የግብይት ገንዘብ እንዳይኖር በማድረግ የደህንነት ስጋትን እንደሚፈታ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተጨማሪም መንግስት የነዳጅ ምርት ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለውን ስርጭት ሂደት መረጃ እንዲኖረው እና ነጋዴዎችም ግብርና ታክስ እንዳያጭበረብሩ በማድረግ ቴክኖሎጂው ትልቅ ሚና አለው ነው ያሉት።