በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ከመንግስት ኮሚኒኬሽን የተሰጠ መገለጫ

መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት አቅጣጫ አስቀምጧል። በዚህ መሠረት የየክልሉን ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችላቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል።

በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት እንደ ምርጫቸውና እንደ ፍላጎታቸው በመከላከያ፣ በፌደራል ፖሊስ ወይም በክልል ፖሊስ አባልነት መካተት ይችላሉ።

በዚህ ሐሳብ ላይም ከልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት ጋር ከመግባባት ላይ ተደርሷል።

ቀደም ብሎም በሁሉም ክልል አመራሮች ጥናት ተደርጎበት፣ በተገኘው ውጤትም ያለምንም ልዩነት ውሳኔውስምምነት ተደርሶበታል ።

ይህ ተግባር እንዲፈፀም መላ ህዝባችንም ሲጠይቅ ቆይቷል። ይሄንን ተከትሎም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

የክልል ልዩ ኃይልን በተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የማካተት ውሳኔና የተግባር እንቅስቃሴ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የሚከናወን ነው። ይህ አካሄድ የኢኮኖሚ ዐቅማችንን በማሰባሰብ የሠራዊታችንን የሥልጠና፣ የትጥቅ እና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ አለው።

ይሄንንበመረዳትም በሁሉም ክልሎች ሂደቱ በመግባባትና በውይይት እየተከናወነ ይገኛል።

ሆኖም በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ፤ በአንድ በኩል የመልሶ ማደራጀት ሥራውንና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሐሰት ወሬ በመጠለፍ ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት
ታይተዋል።

ከሚነዙት የሐሰት አጀንዳዎች መካከል፤ የመልሶ ማደራጀቱ መርሐ ግብር በአማራ ክልል ብቻ እየተካሄደ ነው፤ ሕወሐት ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት የክልሉ ልዩ ኃይል ትጥቅ ይፈታል የሚሉትና
ሌሎችም ይገኙበታል። እነዚህ አጀንዳዎች ሂደቱን ለማደናቀፍ በሚፈልጉ ኃይሎች እየተናፈሱ ይገኛሉ።

የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ፕሮግራም በመላ ሀገሪቱ የሚተገበር ነው።

ሥራውም በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኝነው። ሂደቱንም መንግሥት በጥናት፣ በዕቅድ እና በጥንቃቄ እየመራው ይገኛል።

ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ተግባር በሚፈጸምበት ጊዜ።፣ በክልሎች አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ቦታዎች ሥምሪት ወስዷል።

በሌላ በኩል ሕወሐት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ እየተደረገ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

የሕወሐት ትጥቅ የመፍታት ሂደት በተፈረመው ስምምነት መሠረት ያለማወላወል የሚፈጸም እንጂ ከሌላ ሀገራዊ ዕቅድ ጋር የሚቀናጅም የሚጣረስም አይደለም።

የሂደቱ ዋና ዓላማ የትኛውንም ልዩ ኃይል ትጥቅ ማስፈታት አይደለም።

ልዩ ኃይሉ ትጥቁን ይዞ እና የተሻለ ዐቅም ተፈጥሮለት በምርጫው መሠረት የክልል ፖሊስን፣ የፌደራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀል ማድረግ ነው።

በዚህ ሂደት መካተት የማይፈልግ ማንኛውም የልዩ ኃይል አባል ካለ መብቱ ተጠብቆ ወደ መደበኛ የሲቪል ሕይወት እንዲገባ መንግሥት አስፈላጊውን የማቋቋም ሥራዎች ይሠራል። እንዲቋቋምም ድጋፍ እንደሚያደርግ ያስታውቃል።

የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደራጀቱ ሥራ መንግሥት ለዘላቂ የሀገር ጥቅምና ደኆንነት የወሰነው ውሳኔ በመሆኑ ኃላፊነቱንም በከፍተኛ ጥንቃቄ ይወጣዋል።

ስለዚህ በተለያዩ የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ከሚሠራጩ አሳሳች መረጃዎች በመራቅ መላው ሕዝብ እንዲሁም የክልል ልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት ለመርሐ ግብሩ ስኬት እንዲረባረቡ መንግሥት ያሳስባል።

መጋቢት 28 2015 ዓ/ም

አዲስ አበባ

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት