ሰኔ 03/2013(ዋልታ) – ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰሩ እንዲሁም ለመገንባት እቅድ የተያዘላቸው ፕሮጀክቶች ይፋ ተደርገዋል::
በዚህም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች መልሶ ለማቋቋም የተገነባው የጎበና ቡታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቋል::
በምርቃት ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አርሶ አደሩ ለልማት በሚል እሳቤ ከይዞታቸው ተነስተው ተገቢውን ጥቅም ሳያገኙ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡
መሰል ፕሮጀክቶች ይህን ለመቀየር እና የተማረ ሀይል ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የአርሶ አደር ልጆችም ከዚህ ተቋዳሽ በመሆን ለሀገር የሚጠቅም አበርክቶ እንዲወጡ አሳስበዋል::
አርሶ አደሩም ሀገር የጀመረችውን የልማት ጎዳና ለመደገፍ ላደረገው ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ትምህርት ቤቱም በቀጣይ የትምህርት ዘመን ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እንደሚያስተናግድ ተገልጿል::
በተጨማሪም ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ለመገንባት የታቀደው የእንስሳት እርባታ እና ተዋፅኦ ማእከልም የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል::
የአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ ስራ አስኪያጅ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ የከተማው ማህበረሰብ የጀርባ አጥንት የሆነው እርሶ አደር ከከተማው መስፋፋት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ ስራዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡
የእንስሳት እርባታ እና ተዋፅኦ ማእከልም ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል::
ይህ ፕሮጀክትም የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ጥቅም ከማስከበር ባሻገር የኢንዱስትሪ ባለቤት የሚያደርግም ነው ተብሏል::
መሰል ፕሮጀክቶችም ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ጥቅማቸውን ከማስጠበቅ እንዲሁም በጋራ ለማደግ በሚደረገው ርብርብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተመላክቷል::
እንዲሁም ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች 23 ሺህ ገደማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተላለፉ ሲሆን፣ በቀጣይም በርከት ያሉ የንግድ ሱቆች ለአርሶ አደሮች እንደሚተላለፍም ተገልጿል::
ከ48 በላይ ሱቆች 1.4 ኪሜ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እና 9 ሼዶች በማእከሉ መካተታቸውም ተጠቁሟል፡፡
(በሄብሮን ዋልታው)