ሰኔ 03/2013 (ዋልታ) – የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬና አካባቢው በነበረ የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው ለነበሩ ወገኖች 15 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አየለች እሸቴ እንደገለጹት ድጋፉ የተደረገው በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን ለመቋቋም የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ ነው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከራሱ በተጨማሪ የጤናና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በማስተባበር ያሰባሰበውን ድጋፍ ለወገኖቹ ማበርከቱን አስታውቋል፡፡
ለወገኖቹ ከተደረገው ድጋፍ መካከል የዳቦ ዱቄት፣ ሩዝና ዘይት ምግቦች እንዲሁም የሌሊትና የቀን አልባሳት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የምግብ ማብሰያና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳደሪ ብርሃኑ ታየ በሚኒስቴሩ በኩል የተደረገው ድጋፍ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን ያሳየ በመሆኑ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው የተፈናቃዮችን ስነ ልቦና ለመመለስም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአጣየና አካባቢው የደረሰው ችግር በሰሜን ሸዋ ብቻ ሳይሆን የሀገር ችግር በመሆኑ ሁሉም የሀገሪቱ ህዝብና የልማት አጋሮች ተፈናቃዮችን ለማቋቋምና ከተማውን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።