በአፋር ክልል ነፃ በወጡ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስራ ተጀመረ

ኅዳር 29/2014 (ዋልታ) – በአፋር ክልል ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ የወጡ አካባቢዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ  የጥገና እና  የመልሶ የግንባታ ሥራ መጀመሩን  የክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሲን አሊ እንደገለፁት÷ በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ቡድን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች በመውደማቸው ከአንድ ወር በላይ በክልሉ በአራቱም ዞኖች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋረጦ ቆይቷል፡፡

በወራሪው ቡድን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት በመጠገንና  መልሶ በመገንባት ወደ አገልግሎት ለመመለስ የሚያስችል ዐቢይ ኮሚቴና የቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ነው አቶ ያሲን የገለጹት።

አሸባሪው ህወሓት ወረራ ካካሄደ ጊዜ ጀምሮ በክልሉ በሚገኙ 7 አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ሙሉ በሙሉ ያወደመ ሲሆን÷ በተለይም የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከፍኛ ጉዳት እና ውድመት አድርሷል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ የሚገኙ 15 አገልገሎት መስጫ ማዕከላት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት አቋርጠው መቆየታቸውን ጠቁመው÷ በዚህም ከ23 ሺህ በላይ የድህረ ክፍያ እና ከ5 ሺህ በላይ የቅድመ ክፍያ ደንበኞች፥ በድምሩ 29 ሺህ የሚደርሱ ደንበኞች አገልግሎት ተቋርጦባቸዋል ነው ያሉት፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦ በቆየባቸው ጊዜያት መሰብሰብ የነበረበት ከ88 ሚሊየን ብር በላይ  ሳይሰበሰብ መቅረቱን የክልሉ ኤሌክትረክ አገልግሎት ማሳወቁን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡