በአፍሪካ ሕብረት የሚካሄዳው የግድቡ ድርድር ትክክለኛ የመፍትሄ መንገድ መሆኑን ቻይና አመለከተች

ግንቦት 17/2013 (ዋልታ) – በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሚካሄዳው የሦስትዮሽ ድርድር ትክክለኛ የመፍትሄ መንገድ መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል የልዑክ ኃላፊ ዢ ቲያን አስታወቁ።
ቻይና የህዳሴ ግድብን አስፈላጊነት በውል ትረዳለች ያሉት ዢ ቲያን፣ በአፍሪካ ሕብረት የሚካሄደው የሦስቱ አገራት ድርድር ለመፍትሄው ትክክለኛ መንገድ እንደሆነና ለድርድር ሂደቱም ቻይና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድቡ የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ቀልብ እየሳበ መሆኑን ያስታወሱት ዢ ቲያን፣ እንደ አንድ የአፍሪካ ወዳጅ አገር ቻይና የግድቡ አስፈላጊነት በተለይም ለኢትዮጵያ ልማት ያለውን ጠቃሜታ በውል ስለምትረዳ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደውን ድርድር እንደምታበረታታ አስታውቀዋል።
አካሄዱ መፍትሄ ለማግኘት ትክክለኛ መንገድ መሆኑን ጠቁመው፣ እኛ ለአፍሪካዊ ችግሮችና ጉዳዮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች እንዲያገኙ እንደግፋለን ብለዋል።
እያንዳንዱ አገርም ድርድሩን በሰላማዊ መንገድ በመቀጠል በሦስቱ ወገኖች በኩል ተቀባይነት ያለው መፍትሄ እንዲያገኙ እናበረታታለን ሲሉ ገልጸዋል።
ከሦስቱም ተደራዳሪ አገሮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስላለን ሁሉም አካላት ድርድሩን በሰላማዊ መንገድ እንዲቀጥሉና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እገዛ እናደርጋለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የአፍሪካ ሕብረት ከሚያካሂደው ድርድር እንዳይወጡና ልዩነቱም በውይይት እንዲፈታ ቻይና ትደግፋለች ሲሉም አክለዋል።
ቻይና በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለሚካሄደው የሦስቱ ሀገራት ድርድር ዘላቂ መፍትሄ እንዲያመጣ ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ማስታወቃቸውን ኢፕድ ዘግቧል።