በኢትዮጵያዊ አብሮነትና አንድነት ዙሪያ ለ35 ሺህ ወጣቶች ስልጠና ሊሰጥ ነው

በኢትዮጵያ አንድነትና አብሮነት ዙሪያ ከነገ ጀምሮ ለ35 ሺህ ወጣቶች ስልጠና የሚሰጥ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል አስታወቁ።

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ አባላት አመራሮች በቢሾፍቱ ከተማ ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንዳሉት በኢትዮጵያ አንድነት እና አብሮነትን ለማጠናከር የሚያግዙ የወጣቶች ስልጠና ነገ ይጀመራል።

የመጀመሪያ ዙር ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ 35 ሺህ ወጣቶችም ከነገ ጀምሮ በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ተዘጋጁ የማሰልጠኛ ማዕከላት ይገባሉ ብለዋል።

ለ45 ቀናት ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ለአሥር ወራት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመሰማራት ለማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሏል።

የተጀመረውን የዘላቂ ሰላም ግንባታ ሥራ ከግብ ለማድረስ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ መስራት አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አገር ወዳድና ምክንያታዊ የሆኑ ወጣቶችን በመገንባት ሂደት ከዚህ በፊት ትልቅ ጉድለት እንደነበር ሚኒስትሯ አስታውሰዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።