በኢትዮጵያ በግል የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ለመሳተፍ ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት 850 ሚሊየን ዶላር ለመንግስት ገቢ አደረገ

ኢንጂነር ባልቻ ሬባ

ግንቦት 27/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ በግል የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ለመሳተፍ ጨረታውን ያሸነፈው ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጰያ የተባለው ድርጅት ያሸነፈበትን 850 ሚሊየን ዶላር ለመንግስት ገቢ ማድረጉን የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ።

አዳዲስ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በማካተት ሁለተኛውን ኦፕሬተር ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ በቅርቡ እንደሚወጣም ተገልጿል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የዲጂታል ኢኮኖሚውን ማሻሻል ዋነኛው ጉዳይ ነው።

በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ላይ ደግሞ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ ጉልህ ሚና አለው።

ዘርፉ እ.ኤ.አ በ2030 ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ላይ የ6 ነጥብ 6 በመቶ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በመንግሥት ተይዘው የነበሩ የልማት ድርጅቶችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በቴሌኮም ዘርፍ ልምድና አቅም ያላቸው የውጭ ኩባንያዎችን ለማሳተፍ የተሰራው ስራ ለአብነት ይጠቀሳል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ዘርፉ በውድድር እንዲመራና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ተጨማሪ ሁለት ኦፕሬተሮችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በጥንቃቄ ሲሰራ ቆይቷል።

በዚህ መሰረት ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው ቮዳፎን፣ ቮዳኮም፣ ሳፋሪኮም፣ ሲሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕ የተባሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በጥምረት ያቋቋሙት ኩባንያ ጨረታውን በማሸነፍ ፈቃድ አግኝቷል።

በጨረታ ሰነዱ በተቀመጠው ድንጋጌ መሰረት ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት በሰባት ቀናት ውስጥ የፈቃድ ስምምነት ፊርማውን ከባለሰልጣኑ ጋር የሚፈራረም ይሆናል።

ከዚህ ባለፈ 14 ቀን ባልሞላ ጊዜ ድርጅቱ ጨረታውን ያሸነፈበትን ዋጋ ለመንግስት ገቢ ማድረግ ይጠበቅበታል።

በዚህ መሰረት ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጰያ ያሸነፈበትን 850 ሚሊየን ዶላር ለመንግስት ገቢ ማድረጉን ኢንጂነር ባልቻ ገልጸዋል።

ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት ለጨረታው ማስኬጃ ከእንግሊዝና ከአሜሪካ የፋይናንስ ተቋማት 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር አግኝቷል።

የአሜሪካ መንግሥት አስተዳደር ኢትዮጵያ ላይ ካሳለፋቸው የውሳኔ ሐሳቦች ጋር ተያይዞ በአንዳንዶች ዘንድ በብድር አቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጠራል የሚል ስጋት ያነሳሉ።

ይሁንና የብድር ስምምነት ከተለያዩ ኩባንያዎች ጥምረት ከሆነው አሸናፊ ድርጅት ጋር በመሆኑ ምንም አይነት አሉታዊ ተጽዕኖ አይኖረውም ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

እንዲህ አይነት አሰራሮች ከመለመዳቸው ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድንበር ተሻጋሪ ኢንቨስትመንቱን መጠበቅ የሚያስችል ስምምነት መኖሩንም አንስተዋል።

ባለሥልጣኑ ባወጣው ጨረታ ለመሳተፍ ስምንት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፍላጎት ቢያሳዩም፤ የጨረታ ሰነዳቸውን ያስገቡት ግን ሁለት ብቻ ናቸው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ባለሥልጣኑ በቴክኒክ ስድስት በፋይናንስ ደግሞ ሶስት ጠንካራ መስፈርቶችን ማውጣቱ በምክንያትነት ተነስቷል።

ኩባንያዎቹ ቢያንስ ከ30 ሚሊዮን ያላነሰ ደንበኞች ያላቸው መሆኑ፣ በበለጸጉ አገሮች ብቻ ሳይሆን፤ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ያላቸው ተሳትፎ፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን የማስተዳደር አቅምና የገበያ ድርሻቸው ከመስፈርቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

ከፋይናንስ መስፈርቶቹ መካከል ደግሞ የኩባንያዎቹ አጠቃላይ ሃብት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ፣ ጨረታውን አሸንፈው አገር ውስጥ ሲገበዩ 500 ሚሊዮን ዶላር ማስተማመኛ (ጋራንቲ) ማስቀመጥ አለባቸው የሚሉት ይገኙበታል።

በዚህ መሰረት የጨረታ ሰነዳቸውን ያስገቡ ሁለት ድርጅቶች ቢኖሩም፤ ያስገቡት የጨረታ መወዳደሪያ ዋጋ መለያየትን ተከትሎ ለአንዱ ኦፕሬተር ብቻ ፈቃድ እንዲሰጥ መወሰኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ሁለተኛው ተጫራች ኩባንያ ያለውን ልዩነት አስተካክሎ መግባት የሚችልበት የ10 ቀናት ዕድል የተሰጠው ቢሆንም ኩባንያው ዋጋውን ማስተካከል እንደማይችል አሳውቋል ነው ያሉት።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ሁለተኛውን የቴሌኮም ኦፕሬተር ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው።

በጨረታው ላይ አዳዲስ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የመሰረተ ልማት ዝርጋታው ላይ መሳተፍ የሚችሉበት ዕድል ሊታይ ይችላል።

ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጰያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ከ8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ምዕዋለ ንዋይ የሚያፈስ ሲሆን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።

በመጪው ማክሰኞ አገር አቀፍ ይፋዊ የምስክር ወረቀት ርክክብ ስነ-ስርዓት እንደሚካሄድም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዘርፉን ለመደገፍና ለመቆጣጠር በአዋጅ የተቋቋመ ራሱን የቻለ ተቋም ነው።