ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
አገራዊ የምክክር መድረኮች በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተካሂደው ውጤት እንዳስገኙና ኢትዮጵያንም በየጊዜው ከሚፈራረቅባት የግጭት አዙሪት ሊያወጣት እንደሚችል የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ ገልጸዋል፡፡
የምክክር መድረኩ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር ብቻ የሚገናኝ አለመሆኑንም አብራርተዋል፡፡
እስካሁን መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸውና የኢትዮጵያን ኅልውና የሚፈታተኑ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ በቀጣይ የሚቋቋመው የምክክር ኮሚሽን ችግሮችን በመፍታት ለመጪው ትውልድ ሰላማዊ ሀገር ማስረከብ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
በአዋጅ የሚቋቋመው ኮሚሽን እስከታች ድረስ በመውረድ የሚሰራ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ሕዝቡን በታማኝነት የሚያገለግል እንዲሁም ለኢትዮጵያ አንድነት ዋጋ የሚከፍል ተደርጎ እንዲቋቋም ቋሚ ኮሚቴው በዝርዝር ማየት እንዳለበት በምክር ቤቱ አባላት መነሳቱን ከተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
መንግስት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ይሁኝታ አግኝቶ ሲመረጥ ቃል ከገባባቸው አገራዊ ጉዳዮች መካከል ሁሉን አካታች የሆነ አገራዊ ምክክርና ውይይት በማካሄድ አገራዊ መግባባት እና በአገር ጉዳይ የጋራ አቋም እንዲኖር የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት አንዱ መሆኑ ይታወቃል።