በኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እስኪሳካ ድጋፉን ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ

ሐምሌ 04/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረው ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እስኪሳካ ድጋፉን ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካትሪን ፊኒ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ መንግስት የትምህርት ቤቶችን ምገባ ፕሮግራም ፖሊሲና ስትራቴጂ በማጽደቅ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚመሰገን ነው፡፡

የትምህርት ቤቶች የምገባ መርኃግብር የትምህርት ተሳትፎና የመማር ምጣኔን ከማሻሻል ባሻገር የስርዓተ ጾታን ክፍተት የመሙላት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም ምክትል ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት በጀመረው ብሄራዊ ሀገር በቀል የትምህርት ቤቶች የምገባ መርኃግብር ከግብ እንዲደርስ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በአጋርነት ሲሰራ መቆየቱንም ካትሪን ፊኒ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ጊዜ በየዓመቱ መንግስትና የዓለም ምግብ ፕሮግራም የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ጨምሮ የምግብ እጥረት ባለባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች በትምህርት ቤት ምገባ መርኃግብር   ከግማሽ ሚሊየን የሚበልጡ ተማሪዎችን መድረስ መቻላቸውን አስታውሰዋል፡፡

የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስትር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) የዓለም የምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት በትምህርት ቤቶች ምገባ መርኃግብር እየተሳተፉ የሚገኙ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አመስግነው፣ ድጋፋቸው ለወደፊቱም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡