የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን ጀማሪ ባለሙያዎችና አመራሮች አስመረቀ

ግንቦት 12/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በደቡብ ፖሊስ ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን ጀማሪ ባለሙያዎችና አመራሮችን አስመረቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ የተለያዩ ተቋማት በሪፎርም ሂደቱ አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ተግባር እያከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

ከሪፎርም ስራው አንዱ በጉምሩክ ኮሚሽን በኮንትሮባንድ መከላከል ስራ የሚሳተፉ ጀማሪ ባለሙያዎች በአካል ብቃታቸው የጎለበቱ፣ በሥነ-ምግባራቸው የተመሰገኑና በስብዕናቸው የታነጹ ሆነው ለአገራቸው ብልፅግና በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ፖሊስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ሰልጣኞችን ተቀብሎ የኮሚሽኑን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ካሪኩለም በመቅረፅ ለባለሙያዎቹ ስልጠና መስጠቱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ በተመደቡበት ቦታ መልካም በሆነ ስነልቦና፣ ችሎታ፣ ሥነ ምግባር፣ ሞራል ልዕልና፣ ቅንነት፣ ታማኝነት፣ መልካም አገልጋይነትና ታታሪነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በጥብቅ ዲሲፕሊን መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ተመራቂዎቹ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ያወጣውን መስፈርትና የመግቢያ ፈተና አልፈው ወደ ስልጠና የገቡ የክልሎችና የሁለቱ የከተማ አስተዳደር ሰልጣኞች መሆናቸው ታውቋል፡፡

ተመራቂዎቹ የአካል ብቃት ስልጠና፣ የሕግ አስከባሪ ኦፊሰር ሥነ ምግባር ትምህርቶችን፣ ፖሊሳዊ ሰልፍ፣ የመሳሪያ አያያዝና አጠቃቀም ስልጠናዎችን እንዲሁም የጉምሩክ አዋጅ፣ የአሰራር ደንቦች እና የአፈጻጸም መመሪያዎች ላይ ትምህርት መውሰዳቸው ተገልጿል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት ጄኔራል መኮንኖች፣ የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች መገኘታቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።