በኦሮሚያ ክልል የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት በማስመልከት የሩጫ ውድድሮች እየተደረጉ ነው

መጋቢት 22/2016 (አዲስ ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የሩጫ ውድድሮች እየተደረጉ ነው።

ውድድሩ እየተደረገባቸው ከሚገኙ ከተሞች መካከል ሸገር ከተማ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ ነቀምቴ፣ ነጌሌ ቦረናና አምቦ ይገኙበታል።

በሸገር ከተማ እየተካሄደ ባለው አምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ታዋቂ አትሌቶችና ከከተማው ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አረጋዊ በርሄን (ዶ/ር) ጨምሮ የሸገር ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የመጋቢት ወር እውነተኛ ፌደራሊዝም ዕውን የሆነበት፣ ወንድማማችነትና አብሮነት የተጠናከረበት ወር ነው።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አገራችን በውስጥና በውጭ ኃይሎች ብትፈተንም ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ ፀንተው በመቆማቸው ሀገር አንድነቷ ተጠብቆ በሉዓላዊነቷ ፀንታ መቀጠሏን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት እየሰጠ ባለው ቆራጥ አመራር የህብረተሰቡን ጥያቄ የመለሱ ከ55 ሺሕ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል በቦንድ ግዢና በስጦታ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ አስተዋጽኦ መደረጉን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ 13 አመታትን ያስቆጠረውና በለውጡ አስተዳደር የአመራር ሰጪነት ወደ መጨረሻ ምዕራፍ የተቃረበውን የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍጻሜ ለማድረስ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።