የኢትዮጵያ ካሜራዎች መካኒክ

መዝሃር ሁሴን ይባላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሜራ በመጠገን ለ55 ዓመታት የቆዩ አንጋፋ ባለሙያ ናቸው፡፡ ከካኖን እስከ ሶኒ ፣ ከፓናሶኒክ እስከ ፉጂፊልም እና ሌሎች የካሜራ አይነቶችን ፈተው ሲጠግኑ ወደር የላቸውም ይባልላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ ሚዲያዎች ካሜራቸው የሆነ ነገር ሲሆን የመጀመሪያ ምርጫቸው እሳቸው ናቸው፡፡ በዚሁ ሙያቸውም የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ላይ ተሰልፈው አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡

መዝሃር የዘር ግንዳቸው ከህንድ ይሁን እንጂ እሳቸው ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ቅድመ አያታቸው ኢትዮጵያን የረገጡ የመጀመሪያ ህንዳዊ ናቸው ይባላል፡፡ 12 ቋንቋዎችን መናገር ይችላሉ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ከ55 አመታት በላይ በዚህ ሙያ ላይ የቆዩ ሲሆን በእሳቸው እጅ ያልተነካ የሀገራችን መገናኛ ብዙሐን ካሜራ አለ ለማለት አያስችልም፡፡ አባታቸውና ልጃቸውም ቢሆኑ ከዚሁ ዘርፍ ብዙም ሳይርቁ ታዋቂ ፎቶግራፈር ናቸው፡፡

መዝሃር ብዙ አዳዲስ እውቀቶችን የሚያገኙት ከሚያነቧቸው መጻሕፍት እና ከዩቲዩብ ቪዲዮዎች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በዚህም ጓደኞቼ መጻሕፍት እና ዩቲዩብ ናቸው ይላሉ፡፡

ስራዬን በፍቅር ነው እንጂ እንደሙያ አይቼው አይደለም የምሰራው የሚሉት ባለሙያው ሁሉም ሰው በዚህ መንፈስ መስራት እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ በመጨረሻም ኢትየጵያን እንደሚወዷትና ከሕንድ ጋር ያላት ባህልም ተመሳሳይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡