በከተማዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ሚያዝያ 12/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአሽከርካሪ፣ ተሽከርካሪ ፈቃድና እድሳት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የከተማዋ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ በመተግበሩ የትራፊክ ስርዓትን የማክበር ተግባር መሻሻሉንም የከተማዋ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አደም ኑሪ እንደገለጹት፣ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሽከርካሪ ቦሎ አገልግሎት፣ በመንጃ ፍቃድ እደሳና አዲስ በመስጠት ገቢ ተሰብስቧል።

በዚህም ለ43 ሺህ ተገልጋዮች አዲስ መንጃ ፍቃድ መሰጠቱንና 263 ሺህ የቦሎ አገልግሎት ለተሽከርካሪዎች መከናወኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሰጡት አገልግሎቶች ለመሰብሰብ ከታቀደው 1 ነጥብ 19 ቢሊየን ብር ከእቅድ በላይ በማሳካት 1 ነጥብ 229 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አቶ አደም ጠቅሰዋል።

የገቢ መጠኑ ሊጨምር የቻለው የአገልግሎት ተደራሽነቱ በመስፋቱና በታሪፍ ላይ ቅናሽ በመደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ኢንጂነር ብርሃኑ ግርማ በበኩላቸው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ በመተግበሩ የትራፊክ ስርዓትን የማክበር ተግባሩ መሻሻሉን ጠቁመው፣ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚከሰተው ሞት ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር መቀነሱን ገልጸዋል።

የትራፊክ ፍሰቱን ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራት አራት አደባባዮችን በማሻሻልና በትራፊክ መብራት የመተካት ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

“በተመረጡ የከተማዋ ቦታዎች 20 የእግረኛ ማቋረጫዎችና 2 ነጥበ 5 ኪሎ ሜትር ላይ የመንገድ ዳር መከላከያ ተሰርቷል” ያሉት ም/ዳሬክተሩ፣ የስነ ምግባር ችግር ባለባቸውና የቅጣት ሪከርድ በተመዘገበባቸው አሽከርካሪዎች ላይ ከሦስት ወር እስከ አንድ አመት የሚደርስ እገዳ መደረጉንም አንስተዋል።

ምክትል ዳይሬክተሩ እንዳሉት በዘጠኝ ወራት ከትራፊክ ቅጣት ከ252 ሚሊየን 882 ሺህ ብር በላይ እና ከፓርኪንግ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።

የትራፊክ ደንብ በተላለፉ 1ሺህ 334 የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ጠቅሰዋል።

በከተማዋ ባለቤት አልባ ሆነው የቆዩ 500 ተሽከርካሪዎች በኤጀንሲው መነሳታቸውን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።